የሳንሱሲ-ቡራዩ -ታጠቅ ኬላ የመንገድ ፕሮጀክት መዘግየት በእለት ከዕለት እንቅስቃሴያችን ላይ ጫና እያሳደረብን ነው - የመንገዱ ተጠቃሚዎች

69
ነሀሴ 16/2010 በአዲስ መልክ ሊሰራ የታሰበው የሳንሱሲ - ቡራዩ - ታጠቅ ኬላ የመንገድ ፕሮጀክት መዘግየት በእለት ከዕለት ስራቸው ላይ ጫና እያሳደረባቸው መሆኑን የመንገዱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡ ተጠቃሚዎቹ ለኢዜአ እንደሚሉት መንገዱ በአዲስ መልክ ይሰራል ከተባለ ሁለት ዓመት ቢያልፍም እስካሁን በተግባር የሚታይ እንቅስቃሴ አልተመለከቱም፤ የመንገዱ ጥበትና ብልሽትም ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ዳርጓቸዋል፡፡ በቡራዩ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የሚተዳደረው ጅላሉ ሰኢድ እንዳለው የመንገዱ ብልሽት የ20 ደቂቃውን ጉዞ ከአንድ ሰዓት በላይ አስረዝሞበታል፡፡ ይህም በዕለት ከዕለት ስራው ላይ ጫና እንዳሳደረበት ነው የገለጸው፡፡ በተሸከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው ብልሽት ለስራቸው እንቅፋት ከመሆኑ ሌላ ለተጨማሪ የጥገና ወጪ እየዳረጋቸው በመሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ከመስመሩ እየወጡ  መሆናቸውንም  ነው የተናገረው፡፡ ሌላው አሽከርካሪ ሙስጠፋ ከድርም  መንገዱ ይሰራል ከተባለ ረጅም ጊዜ ቢያስቆጥርም መንገዱን ለመስራት የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዳልተመለከተ ገልጿል፡፡ በቡራዩ ከተማ አስተዳደር የከታ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ደመቀ ገብሬ  በመንገዱ መበላሸት ምክንያት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ቁጥር መቀነሱን ገልጸው ይህም ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ የህብረተሰቡ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አምነዋል፡፡ ለዚህም የወሰን ካሳ ክፍያው በመዘግየቱ በአካባቢው መነሳት የነበረባቸው ቤቶች፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ የቴሌና ውሃ መስመሮች በወቅቱ አለመነሳታቸውን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡ ለስራ እንቅፋት የነበሩ ችግሮች በመቀረፋቸው በቀሪው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ መንገዱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጫሊ ቤኛም የመንገዱ ግንባታ የዘገየው በአካባቢው ለሚገኙ 113 ተነሺዎች በወቅቱ ካሳ ባለመከፈሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለካሳ የሚያስፈልገውን ከ17 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ብር በመልቀቁ በተያዘው ክረምት ክፍያው ተፈጽሞ አካባቢውን ለግንባት ነጻ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡   ከዚህ በተጨማሪ ለመብራትና ውሃ መሰረተ ልማቶች ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉንም ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት፡፡ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እተገነባ ያለው የሳንሱሲ - ቡራዩ- ታጠቅ ኬላ መንገድ ፕሮጀክት 14 ኪሎ ሜትር ይረዝማል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም