የሽብር ቡድኑን ከትናንት በላቀ አንድነት ልንፋለመው ይገባል

118

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህወሓትን የሽብር ቡድን ማጥፋት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት በመሆኑ ከትናንት በላቀ አንድነት ልንፋለመው ይገባል ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ኢትዮጵያውያን የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር በመቃወም፣ ወደ ግንባር በመዝመትና ለሠራዊቱና ለፀጥታ ሃይሎች ደጀን በመሆን ትግሉን በስፋት እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድም የመከላከያ ሠራዊቱን በግንባር ተገኝተው እየመሩት ነው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ ኢትዮጵያውያን በሚያደርጉት ትግል እንደ ድርጅትም እንደ ዜጋም የድርሻቸውን እየተወጡ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ፤ ወራሪው ቡድን ጦርነት የከፈተው ሕዝብን እንደ ጠላት ፈርጆ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት የእድገት፣ የንግድና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ትልቅ ችግር የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ ለመቀልበስ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያ ሁሉ በአንድነት በመቆም ሊታገለው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሀላፊው አክለውም መላው ኢትዮጵያዊያን አሁን እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ በማጠናከርና በሕልውና ዘመቻው የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

ይህም የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ በመግታት ወደ ሠላም መመለስ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

የእናት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ ስብስብ የአውሬነት ባህሪይ ተላብሶ የሚንቀሳቀስ ነው ይላሉ።

አገር ለማፍረስ የሚመጣን ቡድን ለመፋለም "ዓይን ማሸት አያስፈልግም" ያሉት አቶ ጌትነት የመፍትሄው አካል ለመሆን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ለማዋረድ የተነሳውን የሽብር ቡድን አጻፋዊ ምላሽ ለመስጠት ሁሉም መነሳት አለበት፤ ጠሪ እና ተጠሪም ሊኖር አይገባም ብለዋል።

አካባቢህን ጠብቅ

ወደ ግንባር ዝመት

መከላከያን ደግፍ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም