የጅማ አዌቱ ወንዝ አረንጓዴ ልማት ግንባታ ስራ ለሶስት ተቋራጮች ተሰጠ

285

ጅማ ፣ ህዳር 15/ 2014 (ኢዜአ) በጅማ ከተማ የአዌቱ ወንዝ አረንጓዴ ልማት 2ኛ ዙር ፕሮጀክት ግንባታ ስራ ለሶስት ተቋራጮች ተሰጠ፡፡

የጅማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር  ከድር መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቆ ለከተማው ከፍተኛ ውበት ፈጥሯል ።

የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት 2ኛ ዙር የፕሮጀክት ግንባታ ለማስጀመር ስራው ለሶስት ተቋራጮች የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክት ግንባታው በ106 ሚሊዮን ብር የሚካሄድና በዘጠኝ ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን አመላክተዋል ።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ 74 ሜትር ስፋትና 400 ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል ፡፡

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂብ ራያ በበኩላቸው በከተማው ቢሺሼ ገበያ ላይ ከፍተኛ ችግር ሲያስከትልና ነዋሪዎችን ሲያማርር የኖረው የአዌቱ ወንዝ አሁን ላይ ለምቶ  እልባት እያገኘ በመሆኑ ለነዋሪው ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው።

ወንዙ ሳይለማ በመቆየቱ በከተማው ውበት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲያሳድር እንደነበር አስታውሰው በተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት የወንዝ ዳርቻው ለከተማው ትልቅ ውበት መፍጠሩን ተናግረዋል ።

የከተማው ነዋሪ የሀገርን ህልውና ከመታደግ ጎን ለጎን የአዌቱን ወንዝ ዳርቻን በማልማት ለመዝናኛነትና ለከተማዋ ውበት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለማድረግ ለተጀመረው ስራ  ድጋፉን እንዲያጠናክር ከንቲባው ጠይቀዋል ።

ከአዲስ አበባ ሸገር ፓርክና የወንዝ ዳር ልማት በተወሰደ ተሞክሮ የተጀመረው የጅማ አዌቱ ወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ይታወቃል ።