ባለፉት 4 ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

94

ህዳር 14/2014/ኢዜአ/ ባለፉት አራት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ በሰጡት መግለጫ ባለፉት አራት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን፤ ይህም የዕቅዱ 98 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

አገሪቷ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም ይህንን ለመቋቋም በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልፀዋል።  

የተገኘው ገቢ ከግብርና 904 ሚሊዮን፣ ከማኑፋክቸሪንግ 157 ሚሊዮን፣ ከማዕድን 188 ሚሊዮን፣ ከኤሌትሪክ ሽያጭ 30 ሚሊዮን ዶላር መሆኑንም አብራርተዋል።

የወጪ ንግዱን ከማሳደግ አንጻር በዓይነት፣ በመጠንና ጥራት ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ግብረሃይል አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዋጋ ንረት ሳቢያ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል ለመሰረታዊ ሸቀጦች የውጭ ምንዛሬ በመመደብ እና ከቀረጥና ታክስ ነጻ በፍራንኮ ቫሉታና ዳያስፖራ አካውንት አማካይነት ወደ አገር እየገቡ ነው ብለዋል።

በዚህም ለአገር ውስጥ አምራቾች ድፍድፍ የፓልም ዘይት እየገባ መሆኑን፤ በተጨማሪም በግዥ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለሟሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት አራት ወራት የመሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦት ከአገር ውስጥ ምርትና ከውጭ በግዥ 286 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፣ 7 ሚለዮን ኩንታል ስኳር እና 400 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለኅብረተሰቡ መቅረቡን ገልጸዋል።

ተጨማሪ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ጊዜ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ሩዝ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ሆኗል ብለዋል።

ሚኒስትሩ በአምራቾች፣ በኅብረት ስራ ማኅበራትና ሸማቾች የገበያ ትስስር ምርት እንዲቀርብ በማድረግ ገበያውን የማረጋጋት ጥረት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቾችና ሸማቾችን በቀጥታ በሚያገናኙ የቅዳሜና እሑድ ገበያዎች የጥራጥሬ እህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የዱቄት እና ሌሎች ምርቶች ለኅብረተሰቡ እየቀረቡ ነው ብለዋል።

ይህም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ኅብረተሰብ እንዳይጎዳ የሚደረግ ጥረት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም