ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ታላቅ የሞራልና የተግባር መሪ ሆነውናል-የአዳማ አመራሮችና ወጣቶች

83

አዳማ ህዳር 14/2014(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እህመድ ጀግናውን የመከላከያ ሠራዊት ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸው የሞራልና የተግባር ስንቅ ሆኖናል ሲሉ የአዳማ ከተማ ወጣቶችና አመራሮች ገለጹ።

ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡ አመራሮችና ወጣቶች እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሸባሪውና ወራሪውን ህወሓት በግንባር ለመዋጋት መወሰናቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብርና ፍቅር በማሳደግ ለመዝመት አነሳስቷቸዋል።

ወጣት ቱራ ረጋሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲልም የሀገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ያስመዘገቡትን ታሪክ አሁንም ሀገር አፍራሾችን ለመዋጋት መወሰናቸው ዜጎችን ያነሳሳል ብሏል።

''ኢትዮጵያን ከጠላት ወረራ ለመጠበቅ ወደፊት እንጂ፤ ወደኋላ አንልም'' ያለው ቱራ፤''ውሳኔያቸው ፈለጋቸው ተከትለን ለመዋጋት የሞራል ስንቅ ይሆነናል''በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

''እኔ በፊትም ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበርኩኝ። ከነገ ጀምሮ  ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ። ምክንያት ሀገር ስትኖር ነው ሁሉም ነገር የሚኖረው። ሀገር ከሌለ ምንም ነገር የለም'' ሲልም ተናግሯል።

ወጣት ነገሶ ኤዳኤ የከተማዋ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ወደ ግንባር ለመዝመት መነሳቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያን በሕዝቦቿ ትጋት በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር መሆኗን ያልተረዱ አንዳንድ ሀገሮች  የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ለመግታት ዝግጁ ነኝ ብሏል።

ለዚህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የዘመቱትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተከትሎ እንደሚዘምት  አስታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ሀገር ላይ የተቃጣውን የውጭና የውስጥ ወራሪ ሀይሎች ለመመከት ያላቸውን ቆራጥነት ያሳየ ነው ያሉት ደግሞ በአዳማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ቃበቶ ናቸው።

''መሪያችን በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ አደጋ ለመቀልበስና ሀገር ለማዳን ወደ ግንባት መንቀሳቀሳቸው ሀገር ወዳድነታቸውን ከማሳየቱም በላይ፤ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖናል''ብለዋል።

በኢትዮጵያውያን ትግል ከሥልጣን የተወገደው አሸባሪው ቡድን ነፍስ እንዲዘራ የሚሞክሩ የውጭ ሃይሎች ከንቱ ሩጫ በተባበረ ክንዳችን ከምኞት እንዳያልፍ እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሐመድ ጉዬ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ከሀገር በላይ ምንም እንደሌላ ያሳየና የእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች ፍላጎት  ቅዠት የሚያደርግ መልዕክት አስተላልፏል።

አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በጥቁር አፍሪካዊያን ላይ መሆኑን እኛ አመራሮች በሙሉ ወኔና ምሳሌነት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ ተከትለን ወደ ግንባር በመዝመት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

''የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ከአባቶቻችና የወረስነው የጀግንነትና የአልገዛም ባይነት ውሳኔ ነው'' ያሉት ከንቲባው፡የከተማው አመራሮች መሪያችንን ተከትለን ወደ ግንባር እንዘምታለን ነው ያሉት።

ትውልዱ በምዕራባውያንና በተላላኪዎቻቸው የተከፈተብንን ጦርነት በማሸነፍ አንድነቷና ነፃነቷ የተከበረ ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን ብለዋል ከንቲባው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም