የመድሃኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ በጤና ላይ የከፋ ጉዳት ስለሚያስከትል መጠንቀቅ ይገባል

151

ጅማ፣ ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ በሰዎች ጤና ላይ የከፋ ጉዳት ስለሚያደርስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲል በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የደቡብ ምእራብ ቅርንጫፍ ጸህፈት ቤት አሳሰበ።

በባለስልጣኑ የደቡብ ምእራብ ቅርንጫፍ ዓለም ዓቀፍ የጸረ-ተዋህስያን መላመድ የግንዛቤ ሳምንትን ስልጠናዎችን በመስጠት በጅማ ከተማ አክብሯል።

በግንዛቤ ሳምንት ስልጠና ላይ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የመድሃኒት ተቆጣጣሪ ባለሙያ አቶ ፈዬራ ሌንጂሳ እንዳሉት በህክምና ባለሙያ ያልታዘዘ የጸረ ተህዋስያን መድሃኒት መውሰድና ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መጠቀም ጀርሞች/microbes/ መድሃኒቶችን እንዲላመዱ ያደርጋል።

“ይህ ደግሞ ለከፋ የጤና እክል ይዳርጋል” ብለዋል ባለሙያው ።

የተለያዩ ጸረ-ተህዋሲያን እንክብሎችን በዘፈቀደ መውሰድ መድኃኒቶቹ በጀርሞቹ መላመድን ስለሚያስከትሉ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ደባልና በመድሃኒት ለማይፈወሱ በሽታዎች እንደሚዳርግ አመልክተዋል ።

ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድሃኒቶችን የጤና ባለሙያ ሳያማክሩ የሚወስዱ ሰዎች ለጤናቸው በማሰብ መጠንቀቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በመድሃኒት መደብር ውስጥ የሚቀመጡ መድሃኒቶች ስለ አያያዛቸው በቂ ቁጥጥር ካልተደረገ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ባያልፍም ሊበላሹ ይችላሉ ” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ስነ ልክ ኢንስቲትዪት የጅማ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተመስገን ተስፋዬ ናቸው።

“በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የተሳተፋ አካላት በበኩላቸው ብዙም ትኩረት የማይሰጡት ግን ለጤናቸው ወሳኝ የሆነ ግንዛቤ አግኝተናል” ብለዋል ።

የጸረ ተዋህስያን መድሃኒቶች መላመድ የግንዛቤ ሳምንት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 በ69ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ ግንዛቤን በመፍጠር ጉዳቱን ለመቀነስ ታስቦ የተጀመረ ሲሆን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ ሲከበር በሀገራችን ለ6ኛ ጊዜ ታስቧል።