የህዝባችን ድጋፍ ለእኛ ትልቅ ጉልበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዝባችን ድጋፍ ለእኛ ትልቅ ጉልበት ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2014 (ኢዜአ) የህዝቡ ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊቱ ትልቅ ጉልበት መሆኑ ተገለጸ።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በጦር ኃይሎች ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል በህክምና ላይ ለሚገኙ የሰራዊት አባላት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የጦር ኃይሎች ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዶክተር ኃይሉ እንደሻው፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የህብረተሰቡ ድጋፍ ተለይቶን አያውቅም ብለዋል።
ሆስፒታሉ በተለይም አሸባሪውን ህወሃት በመፋለም ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊቱ አባላት የተለያዩ ህክምናዎችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸው "የህዝባችን ድጋፍ ደግሞ ለእኛ ትልቅ ጉልበት ነው" ብለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍም ብርጋዴር ጄኔራሉ አመስግነዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ ለኢትዮጵያ መሞት ማለት ትልቅ ታሪክ መስራት ነው፣ ለአገራቸው መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ ጀግኖች ሁሌም ክብር አለን ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው ከሃዲ ቡድን በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተመከተ መሆኑን ገልጸው ድጋፍና አብሮነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።
በአገራችን ላይ ተላላኪና ደካማ መንግስት ለመመስረት የሚመኙት አገራት በኢትዮጵያዊያን የጋራ ትግል ስለሚሸነፉ ምንም አይነት ዕድል የላቸውም ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለማጥቃት የመጣ ሁሉ ተሸንፎ መመለሱን ያስታወሱት ሚኒስትሯ አሸባሪው ህወሃትና ጀሌዎቹ በእርግጠኝነት ተሸናፊዎች ናቸው ብለዋል።