ሚኒስቴሩ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎትን በአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ለማዳረስ መስራት ይጠበቅበታል

4284

አዲስ አበባ 24/2010 የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች የሚሰጣቸው የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ለማዳረስ የበለጠ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በዛሬው እለት አድምጧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ዩሱፍ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች የሚያከናውናቸውን የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ውጤት ማምጣት ይጠበቅበታል።

በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ማዕከላትና ማህበረሰብ ሬዲዮዎኖች ተከላ፣ በቴሌኮም አገልግሎት ማዳረስና በፖስታ አገልግሎት ማስፋፋት በኩል የተሻለ የእቅድ አፈጻጸም ሚኒስቴሩ ማሳየቱ ተጠቁሟል።

ይሁንና በቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማስፋፋት ሥራ በተለይም በስኩልኔት ቪሳት፣ አዲስ ወረዳኔትና የገጠር ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያለው የዕቅድ አፈጻጻም ዝቅተኛ መሆኑ ተነግሯል።

በቀጣይ ሚኒስቴሩ በሴቶችና ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ለ2ሺህ997 በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጡ የገጠር ኮሙኒኬሽን ማዕከላት ለማቋቋም የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ከተጠሪ ተቋማትና ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት ዋና ሰብሳቢው አስገንዝበዋል።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው መስፍን በበኩላቸው፤ አገልግሎቱን በአርብቶ አደሩና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ከቋሚ ኮሚቴው በተሰጠው አስተያየት መሰረት የሚቀጥል እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት የማስፋፋት ሥራ ለስኩልኔት ቪሳት፣ ለአዲስ ወረዳኔትና ለገጠር ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተዘረጉ የመሰረተ ልማቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በፖስታ አገልግሎት መስክ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አቶ ጌታቸው ጠቁመው በተጠቀሱት አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን መላው የአገሪቱ ህዝብ በቂ እውቀት ኖሮት እንዲጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጡ በገጠር ኮሙኒኬሽን ማዕከላት ለማቋቋም የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ከተጠሪ ተቋማትና ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት ዋና ሰብሳቢው አስገንዝበዋል።

በቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ያሉ ሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑት ሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕቅድ መሰረት እንዲያዘጋጁ፣ የብድር አቅርቦት ችግር እንዳይኖርባቸው ከተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ብድር በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።