እንዳሻው አላዩ በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታውን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል

3204

አዲስ አበባ ነሓሴ 15/2010 በሃንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት ዛሬ በተጀመረው 6ኛው የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው እንዳሻው አላዩ የመጀመሪያ ጨዋታውን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

በቦክስ ውድድሩ እንዳሻው አላዩ በ49 ኪሎ ግራም እንዲሁም ሀና ደረጀ በ48 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያን ወክለው እንደተሳተፉ ይታወቃል።

በ49 ኪሎ ግራም ዛሬ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው እንዳሻው አላዩ ኢኳዶራዊውን ቦክሰኛ ጆናታን ሜርቻንን በነጥብ በማሸነፍ ወደ 16ቱ ውስጥ መግባቱን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

ቀጣይ ጨዋታውንም ከነገ በስቲያ ከአርሜንያዊው ሴይራን ዬጊክያን ጋር እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

እንዳሻው አላዩ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም በአልጄሪያ ርዕሰ መዲና አልጀርስ በተካሄደው ሶስተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በ49 ኪሎ ግራም የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ማስገኘቱን አስታውሰዋል።

በ48 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያን ወክላ የምትወዳደረው ሀና ደረጀ ነገ ከአሜሪካዊዋ ተወዳዳሪ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታዋን እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

ሁለቱ ቦክሰኞች በሃንጋሪው ውድድር መሳተፍ የቻሉት ከሚያዝያ 27 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በሞሮኮ ካዛብላንካ ከተማ በተካሄደው የአፍሪካ የወጣቶች የቦክስ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘታቸው እንደሆነ አስታውሰዋል።

ቦክሰኞቹ ለውድድሩ ቅድመ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ ከነሐሴ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአሰልጣኝ ከድር ከማል አማካኝነት ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነው አቶ ስንታየሁ የተናገሩት።

በሃንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት የሚካሄደው 6ኛው በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቦክስ ኢትዮጵያ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ከምትሳተፍባቸው ስፖርቶች አንዱ ሲሆን የሜዳሊያ ባለቤት በመሆን በቦክስ ስፖርት ውጤታማ እየሆነች መምጣቷም ይታወቃል።