በሃሰት ወሬ ሃገር ለማፍረስ እንጂ ለእውነታ የተለጎሙ ድምጾች

56

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አሜሪካና በሷ የሚዘወረው የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ እያሳረፈ ያለውን ጫና በመቃወም ሁሉንም ጉድ ያስባለ የተቃውሞ ሰልፍ አድርጓል። በትዊተርና በሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾችም #NoMORE  ዘመቻዎችም በስፋት ተስተናግደዋል።

ለእውነት ለመቆምና ኢ-ፍትሐዊነትን ለመቃወም አፍሪካዊ ወይም ኢትዮጵያዊ መሆን የግድ እንዳልሆነም መላው የዓለም እውነት ፈላጊዎች በተግባር አሳይተዋል። “ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው ቶሎ ውጡ”፣ “በኢትዮጵያ አየር ላይ በረራ ማካሔድ አደጋ አለው ተጠንቀቁ”፣ “ዘርን መሰረት ያደረገ አፈና በኢትዮጵያ አለ” የሚሉና ሌሎችን ዓይን ያወጡ የሃሰት ፈጠራዎችን ሲተርኩ የሰነበቱት የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን አፍንጫቸው ስር ስለእውነት ለመመስከር አደባባይ የወጣውን ህዝብ ድምጽ ለመስማት ጆሮም አይንም የላቸውም። እነሱ ጋር የሙያ ስነ-ምግባር ብሎ ነገር የለም።

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሔደ ያለውን የህልውና ዘመቻ ተከትሎ መሬት ላይ ያለውንና የራሳቸውን ዲፕሎማቶች ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊያን የሚያውቁትን ሃቅ እያንሻፈፉ የሃሰት ድርሰታቸውን ሲተርኩ የሚውሉት መገናኛ ብዙሃኖቻቸው የአካባቢውን ሃገራትና መላ ጥቁር ህዝቦችን በማስተሳሰር ወደ አደባባይ ያስወጣው የጸረ እጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ የተቃውሞ ትግል ድምጽ የነሱ የዘገባ ትኩረትም አይደለም። በአግባቡም አልዘገቡትም ማለት ይቻላል።

ሰሞኑን ያሳዩት ማንነታቸውም ይህንኑ የሚያመላክት ነው። ግዙፍ የመገናኛ ብዙሃን ኩባንያዎቻቸው መሰሪ ድርጊት በአደባባይ ሲጋለጥና ሲወገዝ እንዳላዩ እንዳልሰሙ ለማለፍ የሚያደርጉት ጥረትም አሁን ላይ ፈተና እየገጠመው መምጣቱን የሚረዱበት ጊዜ ደርሷል። የአሜሪካኑ ነጩ ቤተመንግስትን ጨምሮ ሁሉም ስፍራ የተደመጠውን፣ የታየውን የጸረ እጅ አዙር ቀኝ አገዛዝና ጣልቃ ገብነት የተቃውሞ ጥሪ ካሜራዎቻቸው ሊያዩዋቸው ባይፈቅዱም እውነት ምንጊዜም ከላይ መሆኗ አይቀርምና ዓለም አይቶታል።

በአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች ከተደረጉ ሰልፎች በተጨማሪ በትዊተር ላይ በተካሄደ ህዝባዊ ንቅናቄ እጃችሁን አንሱ #Handsoff ሀይለ ቃል በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በተደጋጋሚ እንዳጋራው ወይም ሪትዊት እንዳደረገው መረጃዎች ያሳያሉ።

ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፉ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ‘በቃ’ #NoMore እና ‘እጃችሁን አንሱ’ #Handsoff የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ በዋሽንግተን ዲሲ፣ ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ኦስቲን፣ ሂውስተን፣ ቶሮንቶ፣ ኦታዋ፣ ካልጋሪ፣ ዊኒፒግ እና ለንደን ከተሞች የተካሔዱት ግዙፍ ሰልፎች የብዙሃኑን ትኩረት መሳባቸው የግድ ነበር።

በካናዳው ካልጋሪ የተካሔደው ሰልፍ አስተባባሪ በሲቲቪ (CTV News) በኩል እንደተናገረው፤ አብዛኛውን ጊዜ የአፍሪካ ሃገራት ችግር መነሻው የመሪዎቻቸው ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ለሶስት አስርታት ያህል ሃገሪቱን የገዛውን ጨቋኝ ስርዓት በማስወገድ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያሸነፈ መንግስት አለ።

በኦስቲን ቴክሳስ የተካሔደውና ከአካባቢው ኦስቲንና ሳንአንቶኒዮ የተሰባሰቡት የሰልፉ ታዳሚዎች ኢ-ፍትሃዊውንና አሸባሪ ቡድኖችን የሚደግፈውን የአሜሪካንን ድርጊት ያወገዘ እንደነበረ ሲቢሰ (CBS Austin) ዘግቦታል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች ቢኖሩም እኛው በራሳችን እንፈታዋለን በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባታችሁን አቁሙ የሚል መልዕክት የተላለፈበት እንደሆነም ገልጿል።

በመላው ዓለም በሚገኙ በ27 ታላላቅ ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ በርካታ ህዝብ የተሳተፈባቸው ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎች ቢካሔዱም ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ሃሰተኛና የፈጠራ መረጃቸውን በመዘገብ የሚታወቁት የምዕራቡ ዓለም ግዙፍ መገናኛ ብዙሃን የሚገባውን ያክል ሽፋን አለመስጠታቸው የሚጠበቅ ነው።

በየትም ስፍራ ያሉ የእውነት ተሟጋች ሰልፈኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች ያስረገጡት ዋና ጉዳይ በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም በሃሰት ላይ የተመሰረተ ሃገር የማፍረስና የአሸባሪ ቡድኖች አጋርነት እንዲያቆም እጃቸውን እንዲያነሱ መጠየቅ ነው #hands off

ኢትዮጵያዊያን አሁን የገጠመን የውስጥ ችግር በመሆኑ እራሳችን እንፈታዋለን የማንንም ጣልቃ ገብነት አንፈልግም”፣ የራሳችንን ችግር በራሳችን እንድንፈታ ተዉን”፣ “ጦርነቱ እንዲቀጥል አንፈልግም”፣ “ሃገራችንን ወደነበረችበት ሰላሟ መመለስ እንሻለን”፣ “አሜሪካ ጣልቃ ለመግባት የምታደርጊውን እንቅስቃሴ አቁሚ” እና ሌሎችም መልዕክቶች በሰልፎቹ የተላለፉበት ነበር።

በተጨማሪም የጥቁር አሜሪካውያን ጥምረት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት እንደሚያወግዝ ገልጾ ውሳኔዋንና እንቅስቃሴዋን መለስ ብላ እንድታጤነው መጠየቁም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም