እንደ ጉም እየበነነ የመጣው የሀሰት ትርክት

447

የትርክቱ መነሻ

አብዛኛው የዓለም አገራት ጋዜጠኛ በምዕራባውያን ሥርዓተ ትምህርት ተምሮና በዛው ታንጾ ወደ ሙያው የገባ ስለመሆኑ አሌ አይባልም። የበዛው ጋዜጠኛ ምዕራባውያን ማህበረሰቦች ነፃ መሆናቸውንና የምዕራቡ ዓለም የብዙኃን መገናኛዎች ደግሞ ነፃ እና ገለልተኛ እንደሆኑ ለዓመታት ተምሮና ተጠምቆ እንዲያምን ሆኗል። ሌላውም እንዲሁ ከማመን አልፎ በማስረጃነትም ዋቢ ሲያደርጋቸው ቆይቷል።

‘ስለ እውነት ይናገራሉ፣ ኃይለኛውን ተጠያቂ ያደርጋሉ’ የሚለውን ትርክት ለዘመናት አምኖና ተቀብሎ ኖሯል። በጽንሰ ሃሳብ የተነገረውን ምዕራባዊ ትምህርት በተጨባጭ ሲታይ ግን በአብዛኛው የተገላቢጦሽ ሆኖ ይገኛል። ምዕራባውያን የብዙኃን መገናኛዎች ዕውነታን ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ታሳቢ ያደረጉ የሀሰትና የፈጠራ ትርክቶች ላይ ማተኮራቸው ደግም ይህንኑ ያሳብቃል።

የአገራትና የፖለቲከኞች ግላዊ ፍላጎት ከሞራልና ከሥነ-ምግባር ወሰን በላይ አልፎ ሲሄድ የሚዲያ ሴራና ቅሌት ከዚህ ጀርባ ስለመኖሩ ይነገራል። ምዕራባውያን መንግሥታትና የብዙኃን መገናኛ አውታሮችም የድሃው ኢትዮጵያዊ መከራና ስቃይ ሳይሰማቸው ስግብግብ ፍላጎታቸውን በማስቀደም የጀመሩት የሀሰት ትርክትም መነሻው ይኸው ነው።

የሚዲያው የሥነ-ልቦና ጦርነት

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሁሉም ግንባሮች በሚገጥመው ሽንፈት የምጽዓት ቀኑ መቃረቡን የተረዱት ምዕራባውያን የብዙኃን መገናኛ አውታሮች ኢትዮጵያ ላይ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ እና የሥነ-ልቦና ዘመቻ ከፍተዋል። ሽብርተኛውን ከቻሉ በሀሰት ትርክት ለመታደግ ካልቻሉ ደግሞ አገራዊ በጎ ገጽታን ለማጠልሸት የሚዲያ ሴራን አጀንዳ አድርገው እየሰሩበት ይገኛሉ።

የአሁኑ የሚዲያ ዘመቻ የተቀናጀና በአንዳንድ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ጭምር የተደገፈ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። ከዋሽንግተን እስከ ዶሃ፣ ከካይሮ እስከ ኒውዮርክ፣ ከሎንዶን እስከ አትላንታ-ጆርጂያ የተዘረጉ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሀሰተኛና የፈጠራ ዘገባዎችን ሆን ብለው በማሰራጨት ኢትዮጵያን ምድራዊ ሲኦል ለማስመሰል መጣራቸውም ጉድ አሰኝቷል።   

በተለይ “አዲስ አበባ ከበባ ውስጥ ገብታለች” የሚለው የፈጠራ ትርክት አገሪቷ ትርምስ ውስጥ እንዳለች ለማስመሰል የሄዱበት ርቀት አሰፋሪ ሆኖ ዓለምን አነጋግሯል። ሴራው የውጭ አገራት ዜጎች ተዋክበውና ተደናግጠው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ የተዛባ የሥነ-ልቦና ጦርነት መክፈታቸው ሙያዊ ሥነ-ምግባር የራቀው ተግባር በመሆኑ በርካቶችን አስቆጥቷል።

ይህ ሆን ተብሎ እየተደረገ ያለውን የሚዲያ ዘመቻ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ላይ የሚያካሂዱት የፕሮፓጋንዳ እና የሥነ-ልቦና ጦርነት አንድ ገጽታ ብቻ መሆኑን ትውልደ ኢትዮጵያዊት አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ በተደጋጋሚ አስረድታለች።

ከላይ የተገለጸው የከበባ ዘገባም ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ሆን ተብለው የሚሰሩ የሥነ-ልቦና ጦርነት አካል ናቸው ብላለች። አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሚፈጽመው የሽብር ተግባር ባለፈ ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን የሥነ-ልቦና ጦርነት በመክፈት ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ እንዲያጣ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ወቅሳለች።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በ ‘ዘ ቢግ ፎር አጀንዳ’ መድረክ ላይ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ለአፍሪካ ያለው እይታ የተንሻፈፈ ነው ማለታቸውም የይዘቱ ቅኝት የተዛባ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። በዚህም ፕሬዚዳንቱ ምዕራባውያን ሚዲያ ለመረጃ ምንጭነት ‘አልመርጣቸውም’ ሲሉ እረፉት ብለዋል። ይህ ደግሞ የምዕራባውያን ድብቅ ሴራና የፈጠራ ትርክት እንደጉም በኖ እንዲጠፋ የሚያሳስብና አፍሪካውያንም ምን ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው።

የከበባ ዘገባውን በስፋት ካሰራጩት ምዕራባውያን የብዙኃን መገናኛ አውታሮች አንድም ዘጋቢያቸውን ተከባለች ወደ ተባለችው አዲስ አበባ ሳይልኩ መጯጯሃቸው ትዕዝብት ላይ ጥሏቸዋል። የኬንያው ፕሬዚዳንት ትዕዝብትና ቅሬታ እንዳመለከተው የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን ክስተቶችን በስፍራው ሳይገኙ በሀሰት እነሱ በሚፈልጉት ቅኝት ከርቀት የመዘገብ መጥፎ አባዜ አሳሳቢ መሆኑን ነው።

በምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ የሚገለጹ አብዛኛዎቹ የፕሮፓጋንዳ ጥጎች በሀሰት ላይ የተመሰረቱ ትርክቶች ናቸው። ይህ ደግሞ አሸባሪዊውን ህወሓት ከመታደግ ባለፈ አገራዊ ገጽታን በአሉታ ማጠልሸትን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የራዲዮ ስፑትኒክ የፖለቲካ ሚስፊትስ አዘጋጅ ቦብ ሽለሁበር “ዕውነታ፣ ሀሰት እና ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ከብሬክስሩ ኒውስ ጋር በነበረው ቆይታ ምዕራባውያን የብዙኃን መገናኛዎች የኢትዮጵያን ግጭት የሚዘግቡበት መንገድ በታቀደ ፈጠራና ሀሰት የታጀበ አስደንጋጭ ዘገባ መሆኑን ገልጿል።

ጋዜጠኛ ቦብ እንደሚለው አሸባሪው  ህወሃት በፈጸመው ወረራ ምክንያት ከአማራና አፋር ክልሎች ስለተፈናቀሉ ዜጎች ምዕራባውያን የብዙኃን መገናኛዎች አንዳችም ትንፍሽ ሲሉ አይደመጡም። ይልቁንም ስለሚጣለው ማዕቀብ ጉዳይ ሰፊ ሽፋን ሰጥተው እንደሚሰሩ ነው ያስረዳው።

ምዕራባውያን በተለይ የአሜሪካ ግዙፍ ኮርፖሬት መገናኛ ብዙሃን ከወገንተኝነታቸው ባለፈ ሞገደኛና ጠብ ጫሪ ጭምር ናቸው ይላል ጋዜጠኛ ቦብ። ይህን ሲሞግት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪው ህወሓት የሚፈጸሙ የሽብር ድርጊቶችን ለመመከት እርምጃ ሲወስድ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት አስመስለው በመዘገብ ለከፋ ግጭት የማነሳሳት ሥራ መስራታቻውን ያነሳል።

እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን የሚያውቁ ህዝቦች በመሆናቸው እነዚህን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ሴራዎችን በማጋለጥ አንድነታቸውን ማጠናከር መቻላቸው ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሚሆን ድንቅ ትግል ነው ብሎታል።

የሀሰት ትርክቱ አንድምታ

ኢትዮጵያ ላይ የሚካሄዱ የማያቋርጡ ሀሰቶችና ፕሮፓጋንዳዎች ምንን ያሳያሉ? ፀረ-ኢትዮጵያ አስተያየቶችን በየጊዜው በሰዎች ጆሮ ማስተጋባቱ ለምን ይሆን? ሁለት ቁልፍ ምክንያቶች ይህንን ለማብራራት እና ዓውዱን ለማሳየት ይረዳሉ።

አንደኛው የምዕራባውያንን እሴቶች የሚያንፀባርቅ የተለመደ አካሄድን ገቢራዊ ማድረግ ነው። አገራዊ ክብርን አሳልፎ የሚሰጥ አሻንጉሊትና ምዕራባውያን የሚጠመዝዙት ተንበርካኪ መንግሥት በኢትዮጵያ መመስረት ነው። ይህ ደግሞ በቅኝ ባልተገዛች ኢትዮጵያ የማይተገበር ቅዠት ብቻ ነው የሚሆነው።    

ሁለተኛው ምዕራባውያን እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ልማት እንደ ቅንጦት እንጂ እንደ መብት አለመቁጠራቸው ነው። ይህ መብት ደግሞ ለምዕራባውያን በኢኮኖሚም ሆነ በርዕዮተ ዓለም በመገዛት የሚወሰን ይሆናል። ኢትዮጵያ ከዚህ ዓውድ ውጭ በመሆኗ በምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን የፕሮፖጋንዳ እና የሥነ-ልቦና ጦርነት ልትሰቃይ ይገባታል የሚል አንድምታ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።  

ሲጠቃለል

የሀሰት ትርክት ዝንባሌዎች እና የሚያስከትሏቸውን ጫናዎችን ለመመከት አገራት የመረጃ ማጣሪያ (Fact Checking) ማስፋፈት እንሚኖርባቸው የአፍሪካ ስትራቴጂያዊ ጥናቶች ማዕከል ይመክራል። ሀሰተኛ ዘገባዎችን ለማጋለጥና አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ Africa Check, Pesa Check, Media Monitoring Africa, እና iLab ከመሳሰሉ የመረጃ አጣሪ ተቋማት ልምድ በመውሰድ የተጠናከረ ሥራ መስራት ሊተኮርበትም ይገባል። ይህ ደግሞ ነውሩ እየተጋለጠ እንደ ጉም መብነን የጀመረውን የሀሰት ትርክት እርቃኑ እንዲቀር የሚያደርግ ፍቱን ፈውስ ይህናል።

እዚህ ላይ የደቡብ አፍሪካው SABC Africa ቴሌቪዥን መሪ ቃልን ማንሳት ይጠቅማል። መሪ ቃሉም The True African Story በግርድፉ የአፍሪካ ዕውነተኛ ዘገባ እንደ ማለት ነው። ጣቢያው መሪ ቃሉን የመረጠው በምክንያት ነው። ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን የአፍሪካን ትክክለኛ ገጽታና ዕድገት የሚያንፀባርቁ ዘገባዎች ከማቅረብ ይልቅ አፍሪካዊ ዕውነታን አዘውትረው ጥላሸት ሲቀቡ በመታዘቡ ነበር። እናም የአፍሪካን ዕውነተኛ ገጽታን የሚያንጸባርቅ ጠንካራ ቁመና ያለው መገናኛ ብዙሃን በስፋት እንዲኖር መስራት ሌላው አማራጭ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም