የጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞን አጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች የሰላም ጉባኤ አካሄዱ

2585

ዲላ ነሐሴ 15/2010 በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞን አጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ሌላ ግጭት ለመፍጠርና የአካባቢውን ሰላም ለማወክ የሚጥሩ አካላት ተለይተው  ለህግ እንዲቀርቡ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

በአካባቢው የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በጌዴኦ ዞን የገደብ ወረዳና በምዕራብ ጉጂ ዞን የቡሌ ሆራ ወረዳ ነዋሪዎች የሰላም ጉባኤ አካሂደዋል፡፡

ሁለቱን ወረዳዎች በሚያዋስነው ኤዴራ በተባለ ሥፍራ በተካሄደው ጉባኤ ነዋሪዎቹ በአካባቢው የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረውና ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ተመልሰው ሠላማዊ ኑሮ እንዲመሩ በሚያስችሉ ጉዳዮችና ስጋቶች ዙሪያ ተወያይተዋል ፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ሽፈራው ቡቱኬ በሰጡት አስተያየት  የሁለቱ ወረዳ አባገዳዎች ትንኮሳና መሰል ድርጊቶች እንዲቆሙ ተዕዛዝ ቢያስተላልፉም አሁንም “የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስና ሌላ ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ ግለሰቦች” መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግና የተፈናቃዮችን ደህንነት ለማረጋገጥ ያመች ዘንድ መሰል ትንኮሳና ጸብ የሚጭሩ አካላት ተለይተው ለህግ ሊቀርቡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሽመልስ ደስታ የተባሉት አስተያየት ሰጪም  የህብረተሰቡን ሰላም የማይፈልጉ አካላት በፈጠሩት ሁከት የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ገልጸው መንግሥት የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተከታትሎ በህግ ሊጠይቃቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አቶ አብዲዩ በራሶ በበኩላቸው ህዝቡ ተመልሶ ወደ ግጭት እንዲገባ ከሁለቱም ወገን የተለያዩ አሉቧታዎችን የሚያራግቡ አካላት መኖራቸውን ገልጸው ህብረተሰቡ እንዚህን የጥፋት ኃይሎች አሳልፎ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ጉጂ ዞን የቡሌ ሆራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደጉ ቡሳዋ ወደወረዳው የሚመለሱ ተፈናቃዮች ሥጋት ውስጥ እንዳይገቡ በኃላፊነት  እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ወደወረዳው ከተመለሱ ተፈናቃዮች ጋር በየቀበሌው ውይይት እየተካሄደ መሆኑን የገለፁት አቶ ደጉ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በህዝቡ መካከል ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ግለለሰቦች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን የገደብ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ማሩ በበኩላቸው ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ከተመለሱ በኋላ የተረጋጋ ሕይወት እስኪመሰርቱ ድረስ ከቡሌ ሆራ ወረዳ አመራር አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ገልፀዋል ፡፡

የመልሶ ማቋቋም ሥራውም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጠል የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ሁለቱም ህዝቦች እርስ በርሳቸው መጠባበቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በሠላም ገባኤው የሁለቱ ወረዳ አጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎች፣ የፀጥታና የቀበሌና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡