በሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች መማር እንደቻሉ የአሶሳ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ

75
አሶሳ ነሓሴ 15/2010 ከተለያዩ ክልሎች ተወጣጥተው በአሶሳ ከተሰማሩ የሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ጥሩ ተሞክሮና ትምህርት ማግኘታቸውን በከተማዋ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ ወጣቶቹ ለኢዜአ እንዳሉት ከአገልገሎት ሰጪዎቹ በአሶሳ ከተማ በቀጣይ በትኩረት ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ገንቢ አስተያየቶች ማግኘት ችለዋል፡፡ በከተማዋ በወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት፣ በፅዳት አጠባበቅና በሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎ አሰጣጥ  ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ በተግባር በማሳየት ጭምር ትምህርት እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ በአሶሳ ተሰማርተው ሲሰሩ ከቆዩት ከነዚህ  ወጣቶች  የባህል ትስስራቸውን በማጎልበት አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያግዝ መልካም ተሞክሮ አግኝተዋል፡፡ በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አብዱ ኢብራሂም  በሰጠው አስተያየት ከሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች  ጋር ሲሰራ መቆየቱን ተናግሮ በዚህም ፍቅርና አንድነት የተማረበት መረሃ ግብር መሆኑን ገልጿል፡፡ ወጣቶቹ በከተማዋ የሚገኘውን የሼህ ሆጀሌ አልሃሰን የችሎት አዳራሽ በጎበኙበት ወቅት የግቢው ፅዳትና አያያዝ ሊሻሻል እንደሚገባው መጠቆማቸውን አመልክቷል፡፡ በከተማዋ በአደንዛዥ እፅ የተጠቁ ወጣቶችን በስፋት በማየታቸው በከተማዋ የወጣቶች መዝናኛዎችና የቤተ መፅሃፍት አገልግሎት እንዲስፋፋ መስራት እንደሚገባም የሰጡትን አስተያየት ትክክለኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ወጣት ኢክራም አህመድ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ስትሆን ከሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ቡድኑ አባልም ናት፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተወጣጣው ቡድን ጋር በመስራቷ የባህል ትውውቅና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ማግኘቷን ገልፃለች፡፡ በከተማዋ የደረቅ ቆሻሻ ፅዳት ሲያከናውኑ የነዋሪው  ተሳትፎ አናሳ በመሆኑ ስራው የማህበረሰቡ የየእለት ተግባር እንዲሆን ከቡድኑ አባላት በቀጣይ ተሳትፎውን ለማሳደግ እንዲሰሩ የተሰጣቸውን አስተያየት በማሳያነት ጠቅሳለች፡፡ የክልሉ ወጣቶች ማህበር ምክትል ዋና ፀሐፊ ወጣት እርቅይሁን አማረ ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊ  ወጣቶቹ የተገኙ ተሞክሮዎች መሰረት በማድረግ ወጣቱን ባለው አደረጃጀት በስፋት በማሳተፍ እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመምጣት በከተማዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ወጣቶችም ከከተማዋ ነዋሪዎች በተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ  መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም