ኢትዮጵያ የህልውና ትግሉን በአሸናፊነት እንድትወጣ የድርሻችንን እንወጣለን

75

ህዳር 12/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና ትግል በአሸናፊነት እንድትወጣ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን መምህራን ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከመምህራን ጋር ዛሬ መክሯል።

በምክከሩ ላይ የተሳተፉ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህርንና ሌሎች የትምህርት ዘርፉ ተወናዮች ለመከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከቱ የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎችን ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን በውይይታቸው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ህዝቦቿ ደምና አጥንት የቆየች፤ በውጭና በውስጥ ወራሪ ሃይሎች ያልተንበረከከች ታላቅ አገር ነች አሁንም በክብሯ ትቀጥላለች ብለዋል።

"በጀግኖች አባቶች ተከብራ የኖረች አገር መሆኗን ለትውልድ የምናስተምረው ታሪክ በአሸባሪዎች እንዲሻር አንፈቅድም፤ ማንኛውንም ትግልና መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል" ብለዋል መምህራኑ።

መምህራኑ ትውልድ በመቅረጽ፣ ማኅበረሰብ በማንቃት፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማጋለጥና በሌሎች ጉዳዮች ላይም ሚናቸውን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የአሁኑ ትውልድ ነገ በታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን ታሪክ የሚሰራ ትውልድ በማፍራት እንዲሁም በግንባር የህልውና ተግሉን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው መምህራን ኢትዮጵያ ያለችበትን አውድ ተረድተው ሃላፊነታቸውን መውጣት አለባቸው ብለዋል።

በተለይም የመማር ማስተማሩ ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆንና ማኅበረሰቡንም በማንቃት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች እያደረጉ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።                                     

መምህራኑ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጋለጥ፣ የአሸባሪው ሕውሃትና ግብረ አበሮቹን ሴራ ለመታገልና ሌሎች ሃሳቦችን የያዘ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ውይይታቸውን አጠናቅቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም