የህልውና ዘመቻውን እየደገፍን የልማትና የመልካም አስተዳደደር ስራችንን እናጠናክረን

323

ሐረር ህዳር 12 / 2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ የህልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ጎን ለጎን የልማትና የመልካም አስተዳደደር ስራችንን እናጠናክረን ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

“አካባቢያችንን ከአሸባሪዎቹ ህውሃትና ሼኔ እንዲሁም  ከቆሻሻ እናጸዳለን” በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ዛሬ ከማለዳው 11 ሰዓት ጀምሮ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንደተናገሩት በዚህ ፈታኝ ወቅት አገራዊ የህልውና ዘመቻውን ከማጠናከር ጎን ለጎን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎቻችንን በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል።

“ልክ እንደ ቆሻሻ ሁሉ አካባቢያችንን ከአሸባሪዎቹ ህውሃትና ሸኔ የማጽዳቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

በተለይ በክልሉ ቅሬታ ከሚቀርብበት አንዱ የአካባቢ ጽዳት ጉዳይ መሆኑን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዘርፉ ስርዓት ተበጅቶለት ሐረርን ጽዱና ሳቢ የማድረግ ስራ በተቀናጀ መልኩ እንደሚከናወን አመላክተዋል።

ከተማዋ የቱሪስት ማዕከል እንደመሆኗ  ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማጎልበት እንዲሁም  በውስጧ የሚገኙ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲዘልቁ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

ህብረተሰቡ አካባቢውን ከቆሻሻ ነጻ እንዲያደርግ፣ በቆሻሻ አወጋገድ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፍ እንዲሁም ህብረተሰቡ እያከናወነ የሚገኘውን የአካባቢን ሰላም የማስጠበቅ ስራ ለማጎልበት ታስቦ የጽዳት ዘመቻው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የጀመረውን መከላከያ ሰራዊትን የመደገፍ፣ የአካባቢን ሰላም የማስጠበቅና ሌሎች የድጋፍና የልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

“ሐረርን ጽዱና ለቱሪስት ምቹ የማድረግ ስራ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው” ያሉት ደግሞ የሐረር ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢስማኢል ዩስፍ ናቸው።

በከተማ ጽዳት ዘርፍ ከማዘጋጃ ቤቱ ሰራተኞች ባለፈ ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲንቀሳቀስ እየተደረገና ውጤት እየታየ መሆኑን አመልክተዋል።

በጽዳት ዘመቻው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን፣ የክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሃመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።