በምዕራብ ጎንደር ዞን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ577 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ተሰበሰበ

95

መተማ፤ ህዳር 11/2014(ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ከህልውና ዘመቻ ጎን ለጎን የተመረተና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ577 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ሰሊጥ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

ሰሊጡ  በመኸሩ ወቅት ለምቶ  ለፍሬ በመድረሱ  የተሰበሰበ መሆኑ ተመልክቷል።

በዚህም በ137 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ  በአርሶ አደሮችና ባለሃብቶች የለማ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከተሰበሰበው ምር ውስጥ 476ሺህ ኩንታል የሚሆነው በአርሶ አደሮች የተመረተ ሲሆን፣ቀሪው በባለሀብቶች  ነው።

ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ሰሊጥ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰበሰብም ባለሙያዎች ድጋፍ ማድረጋቸው አቶ ሞገስ አስረድተዋል።

በዚህም ጥራት ብቻም ሳይሆን ምርቱ  ካለፈው የምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀር በ154 ሺህ ኩንታል ጭማሪ እንዳለው ነው የተመለከተው።

በመተማ ወረዳ የኮኪት ቀበሌ አርሶ አደር ጌጡ ለገሰ፤  በ2013/14 የምርት ዘመን አራት ሄክታር መሬት በማልማት 15 ኩንታል ሰሊጥ ማግኘታቸው ገልጸዋል።

ካገኙቱም የሰሊጥ ምርት ውስጥ አንድ ኩንታል በ7 ሺህ 200 ብር በመሸጥ ባለፈው ዓመት ካገኙት በተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ካለሙት መሬት 36 ኩንታል ሰሊጥ ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በመተማ ወረዳ የደለሎ የእርሻ ልማት ጣቢያ ያለሙት ባለሃብቱ አቶ አዳነ በሪሁን ናቸው።

ምርቱ አሁን ባለው የሰሊጥ ዋጋ ተጠቃሚ ያደርገኛል ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት 413 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ተመርቶ ለውጭ ገበያ መቅረቡን ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም