''አሸባሪው ህወሓት የአሻጥርና የውሸት አርበኛ እንጂ፤ የውጊያ ጀግና አይደለም!''

80

ጋምቤላ፤ ኅዳር 11/2014 (ኢዜአ)''አሸባሪው ህወሓት የአሻጥርና የውሸት አርበኛ እንጂ፤ የውጊያ ጀግና አይደለም!'' በማለት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የሃምሳ አለቃ ዘለቀ ደበሌ ናቸው።

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪው የቀድሞ ሠራዊት አባል ሐሳብን ሌሎች ሁለት የቀድሞ ሠራዊት ባልደረቦቻቸው ይጋሩታል።

አሸባሪው ህወሓት አሻጥርና ውሸትን የተካነ እንጂ፤የጦር ሜዳ ጀግና እንዳልሆነ ቀድሞም ቢሆን ጠንቅቀን እናውቃለን ይላሉ።

የሃምሳ አለቃ ዘለቀ የቀደመውን ትተው የቅርቡን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ያነሳሉ።

ሚሌን እንደያዙ አድርገው የሚያራግቡት ወሬ የውሸታቸው መገለጫ መሆኑን በማሳያነትም አቅርበዋል።

እናም ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ቡድን ወሬ ሳንደናገር ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን በአንድነት መታገል ይገባናል ብለዋል።

ወታደር ሱሌማን ጀርጃር የሃምሳ አለቃ ዘለቀን አስተያያት ይጋራሉ። የሽብር ቡድኑ ፊት ለፊት የመዋጋት ብቃትም ጀግንነትም የለውም ባይ ናቸው።

''በደርግ ጊዜ ተዋግተው ሳይሆን፤ በአሻጥርና የሐሰት ወሬዎችን በመንዛት የሥነ ልቡና ተጽዕኖ ፈጥሮ እንጂ፤ በውጊያ አላሸነፈም''ይላሉ።ከ30 ዓመታት በፊት የሆነውን እያስታወሱ።

አሁንም የተለመደውን ስልታቸውን ለመጠቀም እየሞከሩ መሆናቸውን በመረዳት ሕዝቡ እንዲዋጋው ጠይቀዋል ወታደር ኡስሌማን።

ሌላው የቀድሞው የሠራዊት አባል የ10 አለቃ ፈንታሁን አራጌ የአሸባሪው ህወሓትን ባህርይ በሚመለከት ከሁለቱ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው።

በአሻጥር፣ በተንኮል፣ በደባና በሐሰት ተክኖ የራሱን ፍላጎትና ጥቅም ለማሟላት የሚተጋ አደገኛ ቡድን መሆኑን ይገልጻሉ።ዛሬም ከዚያው ባህርይ እንዳልወጣ በማመላከት።

አባላቱ የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ቡድኑ በአሜሪካና በምዕራባዊያን ጥቅም ተደልሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የገባውን ቃል ለመፈጸም የትግራይ ክልል ታዳጊ ወጣቶችን የሚያስጨፈጭፍ ዓላማ ቢስ እንደሆነም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ በመቀበል ቡድኑን ለመደምሰስ በአንድነት እንነሳ ብለዋል ሦስቱ የቀድሞ ሠራዊት አባላት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም