አርሶ አደሩ ምርት ለገበያ በሚያቀርብበት ወቅት ጠብቀው ህገወጥ ደላሎች የሚፈጥሩት ችግር ሊገታ ይገባል

67

ሶዶ፣ ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህገወጥ ደላሎች አርሶ አደሩ ምርት ለገበያ በሚያቀርብበት ወቅት ጠብቀው ያልደከሙበትን ለማገኘት በግብይት ወቅት የሚፈጥሩት ችግር እንዲገታ ተጠየቀ። 

የደቡብ ክልል ከፍተኛ  የስራ አመራሮች በወላይታ ዞን የግብርና ስራዎች ያሉበት ደረጃ ጎበኙ።

በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በተደረገ ጉብኝት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ይገዙ እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ ለፍቶ ያመረተውን ለገበያ በሚያቀርብበት ወቅት ጠብቀው ያልደከሙበትን ለማግኘት ህገ ወጥ ደላሎች እየፈጠሩ ይገኛሉ።

በህገወጥ ደላሎች የሚፈጠረውን የግብይት ስርዓት እንዲስተካከል ማድረግ የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

"አርሶ አደሩ በሀገራዊ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ነው" ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ የዞኑ አስተዳደር ማነቆዎችን በማስወገድ አምራቹ  የላቡን ዋጋ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩሩ በበኩላቸው፤ የዞኑ ስራ አመራሮች ከአርሶ አደሩ ጋር በመናበብ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ባደረገው ድጋፍ ደጀንነቱን ያሳየ የሀገር ባለውለታ መሆኑን ጠቁመው፤ ውጤታማ የሚያደርግ ግልጽ ግብ በማስቀመጥ አርሶ አደሩ ኑሮው የሚቀየርበት አሰራር መዘርጋት ይገባል ነው ያሉት።

የምርትና የፍላጎት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ የሚነሱ እጥረቶች ለማቃለል  የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች መጠቀምና ምርት የማሻሻል ስራው ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

በዚህም ምርት በብዛትና ጥራት ለገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ገልፀው፤ አስፈላጊ ግብዓቶችን ከማሟላት አንፃር የክልሉ መንግስት እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም