ባንኩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች 8 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት አቅዷል

92

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2014 በጀት ዓመት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሚሳተፉ ባለሃብቶች 8 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ማቀዱን ገለጸ።

የወለድ ማበረታቻና የእፎይታ ጊዜ ላለው ብድር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በሊዝ እና በፕሮጀክት ፋይናንስ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሚሳተፉ ባለሃብቶች 8 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ ዘርፍ ለ5 ሺህ 800 ወጣቶች ሥልጠና እንደሰጠና ዕቅዳቸውን በማየት ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ብድሩን ለመስጠት መመዘኛ መሥፈርቶች እንዳሉትና በሊዝ ፋይናንስ ከሆነ የመሥሪያ ቦታ እና የመሠረተ ልማት ግብዓቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የመሥሪያ ቦታና የመሠረተ ልማት ግብዓቶች መዘግየት መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር ዮሐንስ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመስሪያ ቦታ በወቅቱ እንዲያዘጋጁ አመልክተዋል።

የወለድና የእፎይታ ጊዜ ያለው ብድር በማመቻቸትና ከመደበኛው የብድር አሰጣጥ ዝቅ በማድረግ አዲስ ባለሃብቶችን ለመሳብ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም በኢንዱስትሪ ልማት ግብዓትነት በተለዩ በቅባት እህል፣ በቢራ ገብስና ስንዴ ምርቶች ላይ ለማገዝ ከመደበኛው ተመን በመውረድ ብድር ለመስጠት መታሰቡን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በ2014 በጀት ዓመት የማይመለስ ወይም መመለሱ አጠራጣሪ የሆነ /የተበላሸ/ ብድር 4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ተናግረዋል።

ባንኩ የተበዳሪዎችን ተበድሮ አለመክፈል ልምድ ለማስቀረት እንዲሁም ግልፅና ቀልጣፋ አሰራር ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2013 ዓ.ም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ 8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እንደነበር ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም