ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ዲፕሎማት ሆኖ ሊሰለፍ ይገባል

60

ሀዋሳ ፤ ህዳር 10/2014 (ኢዜአ) ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በማስከበር ጉዳይ ዲፕሎማት ሆኖ ሊሰለፍ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስገነዘቡ።

በዲጂታል ዲፕሎማሲው ዜጎችን በስፋት በማሳተፍ  ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ሚና የሚኖረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት "የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል" ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቷል።

በዚህ ወቅት አምባሳደር ዲና ፤ በኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ከታላቁ  ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ያጋጠመንን ተግዳሮት ለመቀልበስ ታስቦ ምሁራንና አርቲስቶችን በማሳተፍ ከተጀመረ አስር ዓመታት ሆኖታል ብለዋል።

በነዚህ ዓመታት በተካሄደው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በተለይ  በህዳሴ ግድብና በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ከህልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ እየደረሰ ያለውን ያልተገባ ጫና  በፅናት ለመቋቋም አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።

ይህን እንቅስቃሴ ለማጠናከር መንግስት በልዩ ትኩረት  እየሰራ  እንደሚገኝ ያመለከቱት አምባሳደር ዲና፤  በዚህ ረገድም ሁሉም ዜጋ የሀገሩን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ዲፕሎማት  ሆኖ ሊሰለፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ለዚህም ስራ መጠናከርና መስፋፋት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የጀመረውን ዓይነት ጥረት ለሁሉም አቻ ተቋማት ተምሳሌት ስለሚያደርገው ሊበረታታ እንደሚገባው አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ሀገሪቱ ካጋጠሟት ፈተናዎች ውስጥ  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል  የሰላም እጦትና የቀይ ባህር አከባቢ የሀያላን ፍላጎትን አመላክተዋል።

በተለይ በህዳሴ ግድብ ላይ ግብጾች ውሃውን የራሳቸውን አድርጎ የዓለምን እይታ ለመቀየር የሚያደርጉት ትግል፣ ሱዳኖች ደግሞ ግድቡ  ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ቢያውቁም አቋማቸውን በማዋዥቅ  ሀገራችንን ለማደናቀፍ እየጣሩ ነው ያሉት።

የምዕራቡ ሃያላን ሀገራትም የኤዴን ባህረ ሰላጤ  ሰርጥ፣ ቀይ ባህርና ሜዲቴራኒያን ባህር አካባቢ በመያዝ የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በሚያደርጉት  ሽኩቻ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ጠንካራ መንግስት አለመፈለጋቸው ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን ነው የሚያወሱት።

እነዚህን ተግዳሮቶች የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ሳይበገሩ ለመቋቋም እንዲያግዝ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር   አሳታፊ የሆነ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን አጠናክሮ ወደ ተግባር መግባት ጊዜው የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ዓይነት ጥረት በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማዳበር የሚሰራበት አደረጃጀት ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

የሀገራችን ጠላቶች የውስጥ ድክመትን እንደ መሳሪያ ይጠቀማሉ ያሉት አምባሳደሩ ፤ዜጎች ይህንን ተረድተው ለመከላከል  አጥጋቢ ምላሽ እንዲሰጡ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ ፤ ተቋሙ የሀገር ህልውናና ብሄራዊ ጥቅም በሚያስከብር ስራዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሆኖም የህዳሴ ግድብ ግንባታንና  ሀገር ተገዳ የገባችበትን የህልውና ዘመቻ ን በማዛባት  እየዘመቱብን ይገኛሉ፤ ይህም ሴራ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ በእጅጉ  እየጎዳ  ነው ብለዋል።

ይህንን ለመቀልበስ መላው ኢትዮጵያዊያን  በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተጽዕኖ ፈጣሪ የዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን  እውነታውን ለዓለም  በማስገንዘብ  የሀገር ህልውናና ጥቅም ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህንን ተሳቢ በማድረግ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል በዩኒቨርሲቲው መክፈት ማስፈለጉን ገልጸዋል።

በማዕከሉ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚየዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ዕውቀት የሚበለጽግበትና አንድነታችንን በማጠናከር ለሀገር ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ የሚበረከትበት ዕድል የሚያሰፋ መሆኑንም አብራርተዋል።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሪካል ኢንጂነርንግ ትምህርት ክፍል መምህር ይግረማቸው እሼቴ በሰጡት አስተያየት፤ አሁን ላይ ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አንጻር ኢትዮጵያዊያን ኋላቀር ነን ነው ያሉት።

በተለይ በአባይ ዙሪያ የግብጽ ተጽዕኖን በመመከት ዕውነታውን ለማሳወቅ የአባይ ልጆች የሚል ሶፍት ዌር ማበልጸጋቸውን ተከትሎ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙ ዜጎች ስለሀገራቸው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሙጉት ከማድረግ አንጻር ብዙ ይቀራናል ብለዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሙሉ አቅሟን አሟጣ ተጠቅማ ለመልማት የሚታደርገውን ጥረት ለማምከን የሚደረገውን ሴራ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ሁሉ ዲፕሎማት ሆኖ መመከት ይገባል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በምርምር ረገድ ያለውን ሰፊ ልምድ በመጠቀም አከባቢው ያለው የሰው ሃይል አስተባብሮ ለሀገሩ ዲፕሎማት ከማድረግ አንጻር ማዕከሉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ዮሐናን ዮካሞ ናቸው።

በዩኒቨርሲቲው የኢንፌርሜሽን ቴክኖሎጂ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ኤፍሬም ለማ ፤ በአባይ ላይ ግብጽ በሀሰት የሰራችውን ፕሮፖጋንዳ ለመቀልበስ ዕውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃ ለዓለም ለማሳወቅ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ወሳኝነት አለው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም