አሸባሪው ህወሓትን ለመደምሰስ ተዘጋጅተናል-የሐረሪ ክልል ሴቶች

71

ሐረር ህዳር 10/ 2014 (ኢዜአ) በሴቶችና ህጻናት ላይ ግፍ የሚፈጽመውን አሸባሪው ህውሓትን ለመደምሰስ መዘጋጀታቸውን የሐረሪ ክልል ሴቶች አረጋገጡ።

የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የተሳተፉት ሴቶች እንደተናገሩት ሴቶችንና ህጻናትን ለስቃይ የዳረገውን አሸባሪው ህወሐትን በመደምሰስ የኢትዮጵያ ህልውናን ለማረጋገጥ መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው።

ወይዘሮ እድላዊት ፍሬው በሰጡት አስተያየት አሸባሪው ህወሓት በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ እናቶች፣ ህጻናትና አረጋውያን ላይ የፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ከማውገዝ በላይ፤ የሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በስንቅ፣ በትጥቅ፣ ደም በመለገስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።  

ወይዘሮ የኔነሽ ዳኜ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበርና የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚሰለፉ አስታውቀዋል።

''ስንቁንም ልብሱንም ይዤ ወደ ግንባር ለመሄድ ተዘጋጅቻለሁ፤ ባለኝ አቅምም እዋጋለሁ፤አንድ ልጄንም አሁን ለግዳጅ ለመላክ ቃል እገባለሁ'' ብለዋል።

''ኢትዮጵያን ለማዳን ወደፊት እንጂ፤ ወደኋላ የምለው ነገር የለም'' የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ፣  ሀገራችን ዛሬም ጠላቶቿን እየደመሰሰች ህልውናዋን እንድታስቀጥል የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በወንድማቸው ላይ በፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መልሶ እየወጓቸው መሆኑን በመግለፅ አስተያየታቸውን የጀመሩት ወይዘሮ ሂንዲያ አብዲ ናቸው።

ግፈኛውንና ወራሪውን ህወሓት መዋጋት ወንድማቸው ብቻ ሳይሆኑ፤ እሳቸውም ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ''ባለኝ አቅም ሁሉ እነርሱን እፋለማለሁ'' በማለት።

የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አረፋት ኢብራሂም የክልሉ ሴቶች ሳንፈልግ የገባንበትን ጦርነት በድል ለመቃጨት ሚናችንን ማሳደግ አለብን ብለዋል።

በዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለማጠናከር የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሐመድ የክልሉ ሴቶች ሀገር የሚያፈርስ፣ እናትን የሚደፍር፣ ህጻናትን የሚያርድና ንብረት የሚያወድም የሽብር ቡድንን ለማጥፋት ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀዋል።

አሸባሪው ህወሓት ጦርነት ከከፈተበት ወቅት ጀምሮ በስንቅ ዝግጅት፣ በገንዘብና በጉልበት እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነው፤ ቡድኑን ለማጥፋት በተባበረ ክንድ የተጀመሩት የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም