የጸጥታ ሃይሉ የተቀናጀ ውጊያ የ'ካሳ ጊታ'ን ምሽግ መስበር አስችሏል

103

ህዳር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጸጥታ ሀይሉ የተቀናጀ ውጊያ ወሳኝ የሆነውን የካሳ ጊታ ምሽግ መስበር አስችሏል ሲሉ በካሳ ጊታ ግንባር የተሰለፉ የጸጥታ አመራሮች ገለጹ።

አሸባሪው ህወሓት በባቲ በኩል ወደ ሚሌ ለመቁረጥ በማሰብ ያለውን ሃይል ሁሉ አሰባስቦ በካሳ ጊታ ግንባር ጦርነት መክፈቱ ይታወቃል።

ይሁንና የመከላከያ ሠራዊት፣ የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ባካሄዱት የተቀናጀ ውጊያ አሻባሪው መሽጎበት የነበረውን የ'ካሳ ጊታ' ምሽግ በቁጥጥር ስር አድርገውታል።

የካሳ ጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ አህመድ ኑር ሳሊም እንደሚሉት፤ ጠላት መሽጎበት የነበረው ከፍተኛ ተራሮች በጸጥታ ሀይሎች እጅ ገብቷል።

ሁኔታው ጠላት እጅ ከመስጠት ውጪ  ሌላ አማራጭ እንዳይኖረው ያደረገ ክስተትና ከፕሮፓጋንዳ ውጪ ምንም አቅም እንደሌለው የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ሕዝቡ ተቀናጅተው ባደረጉት ውጊያ የተገኘ ድል መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ቢላይ አህመድም የአሻባሪው ትልቅ ምሽግ መሰበሩን ተናግረዋል።

“የካሳ ጊታ ግንባር እጅግ ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር በጸጥታ ሀይሎች የተቀናጀ መናበብና መተጋገዝ ድሉን ማግኘት አስችሏል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም የአሸባሪው ታጣቂዎች አስፈላጊውን ቅጣት አግኝተው በየጢሻው እየተሽሎኮሎኩ እንደሚገኙ ነው የጠቀሱት።

''ካሳ ጊታ አሻባሪው አለ የተባለውን የሰው ሀይልና ሎጂስቲክስ ያሰለፈበት ግንባር ነበር'' የሚሉት ደግሞ  የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ መዲና መሓሙድ ኢብራሒም ናቸው።

የካሳ ጊታ ምሽግ መሰበርም በአሻባሪ ቡድኑ ታጣቂዎችና መሪዎች ትልቅ የሞራል ኪሳራ የሚያስከትል መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም የአፋር ሕዝብና የጸጥታ ሀይሉ ኢትዮጵያን አስቀድሞ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ሆኖ አስፈላጊውን መሰዋዕትነት እየከፈለ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በክልሉ አፍዴራ ወረዳ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑትና በውጊያ እየተሳተፉ ያሉት አቶ መሓመድ አሊ በበኩላቸው የጸጥታ ሀይሎቹ የተቀናጀ ውጊያ በአጭር ጊዜ ድል ለመቀዳጀት አስችሏል ነው ያሉት።

''ወደ ፊትም ከአባቶቻችን የወረስነውን የድል ታሪክ ለማስቀጠል ምንም የሚያግደን ነገር የለም'' ብለዋል አቶ አህመድ።

በዚሁ ግምባር ያለው የሚሊሻ አባላት የሚሰጣቸውን ሀላፊነት እየተቀበሉ አስፈላጊውን መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መናቸውንም ተናግረዋል።

የካሳ ጊታ ወሳኝ ምሽግ ሲደረመስ የጸጭታ ሀይሎቹ በርካታ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያችም ተማርከዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም