ኢትዮጵያን በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በሰፊው ተጠቃሚ የሚያደርግ የወደብ ልማት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

189

ህዳር 10 / 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ከዘርፉ በሚገኝ የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ የወደብ ልማት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የአትክልት፣ ፍራፍሬና ሆርቲካልችር ልማት የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሚመለከታቸው የዘርፉ አጋር አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን በአትክልትና ፍራፍሬ ብሎም ሆርቲካልቸር ልማት በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው የተባለለት ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።ፕሮጀክቱ “ኩል ፖርት አዲስ ”የተሰኘ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቆያና መጓጓዣ ወደብ ግንባታ ሲሆን ወደቡ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ መንገድ ለአትክልት፣ ለፍራፍሬና ሆልቲካልቸር ምቹ የሆነ መሠረተ ልማትን የሚያሟላ መሆኑ ተገልጿል።

ሞጆ በሚገኘው ደረቅ ወደብ የሚገነባው ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በሰፊው የሚመረተውን የአትክልት፣ ፍራፍሬና ሆርቲካልችር ምርት ወደ ተለያዩ የዓለም አገሮች በመላክ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ተመልክቷል።

በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን ከሀገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ በውጭ አገራት ከሚገኙ የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሣድግና የኢትዮጵያን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በተለያዩ የአለም ክፍሎች ጥራታቸው እንደተበጠቀ ማድረስ ያስችላል ተብሏል።

በኢትዮጵያና በኔዘርላንድስ መንግስት በጋራ የሚከናወነው ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በምትልካቸው ምርቶች ተወዳዳሪ እንድትሆን ትልቅ አቅም የሚፈጥርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያስገኝ መሆኑ ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ በኩል ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ቅድሞ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ለኢዜአ ገልጿል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።