የምዕራባውያን የሀሰት ዘገባ ለመቀልበስ የኢትዮጵያን እውነት ለአለም ማስረዳት ይኖርብናል

93

ዲላ ፤ ህዳር 10/2014 (ኢዜአ) በምዕራባውያን የተቃጣብንን የመገናኛ ብዙሃን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለመቀልበስ የኢትዮጵያን እውነት ለአለም ህብረተሰብ በተገቢው ማስረዳት ይኖርብናል ሲሉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ምሁራን ተናገሩ።

የሀሰት ዘመቻው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያላትን ተቀባይነት በማሳጣትና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን ዓላማ ያደረገ ነው።

ምሁራኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳመለከቱት፤ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቦታ መስጠት አያስፈልግም።

በዩኒቨርሲቲው የጋዘጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ሄኖክ ንጉሴ ፤ የውጭ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ጦርነት መክፈታቸውን ይናገራሉ።

የተዛቡ መረጃዎች የውስጥ አንድነታችን ላይ የሚያደርሱትን ጫና ለመቀልበስ የኢትዮጵያን እውነት መሰረት በማድረግ የተጣራ መረጃ ለማድረስ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

በተለይ እውነታን መሰረት ያደረጉ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የጠራ መረጃ በማስረጽና ለምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን ጆሮ ባለመስጠት  የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን ልንከላከል ይገባናል ነው ያሉት።

የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን የሐሰት ፕሮፓጋንዳን ስልት በመጠቀም ጫና ለማሳደር እየጣሩ መሆናቸውን የተናገሩት  ምሁሩ፤በተለይ አሸባሪው ህወሃት በ1983 ሥልጣን ከመያዙ በፊት የተጠቀመበትን  ስልት ዛሬም ለመጠቀም  ሲሞክር  ይታያል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ከታሪክ በመማር በፕሮፓጋንዳውም ሆነ በግንባር በሀገር ላይ እየተቃጣ ያለው ጥቃት ለመመከት  በአንድነት መቆም እንደሚኖርብን  ነው ያመለከቱት።

አሜሪካን ጨምሮ በአንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ለማድረግ ከሚሞክሩት የኢኮኖሚና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ጋር በማያያዝ የእነሱ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት መምህር አስናቀ እንድሪያስ ናቸው።

በዚህም የአሸባሪውን ቡድን ከመደገፍ ባለፈ ሀገራችን በዓለም ያላትን ተቀባይነት በማሳጣትና ጫና እንዲበዛባት በማድረግ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

ይህንን ለመቀልበስ መሰል ጫናዎችን ተቋቁመው ካለፉ ሀገራት በመማር አንድነታችንን በማጠናከር ለሉአላዊነታችን ዘብ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ስሪት ጠንካራ በመሆኑ በፈተና ውስጥ በጽናት ማለፍ የምንችልበትን ሥነ ልቦና በማዳበር  ሀገራዊ አንድነታችንን ለማጎልበት እንድንችል ጠንክርን መስራት ይኖርብናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም