አሸባሪው ህወሓትና ግብረአበሮቹ ወረራ በፈፀሙባቸው አካባቢዎች ከ1 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት ወድመዋል

69

ህዳር 10/2014 (ኢዜአ)  አሸባሪው ህወሓትና ግብረአበሮቹ ወረራ በፈፀሙባቸው አካባቢዎች ከ1 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት መዘረፋቸውንና መውደማቸውን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
 ሚኒስቴሩ አንፃራዊ ሠላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች የሚገኙ 20 የጤና ተቋማትን በድጋሚ ስራ ማስጀመር የሚያስችል ግብዓት መላኩንም አስታውቋል።

አሸባሪው ህወሓት በየደረሰባቸው አካባቢዎች በተለይ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

የሽብር ቡድኑ ዓላማ ሕዝብን መጉዳት በመሆኑ እናቶች የሚወልዱባቸውን፣ ሕፃናት የሚታከሙባቸውን የጤና ተቋማት በማውደም ክፋቱን በተግባር አሳይቷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጤና ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸሙንና የሕክምና ቁሳቁስ መውደማቸውን፤ በዚህም በርካታ ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ወረራ ከተፈጸመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በተጨማሪ የጸጥታ ችግር ባለባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችም በተመሳሳይ በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

በተደረገው ማጣራት በጤና ጣቢያ ደረጃ ብቻ ከ1 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል፤ ውድመትም ደርሶባቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የጤና ተቋማትን ማውደም አግባብ አለመሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ የወደሙ ተቋማትን እንደገና ለማቋቋም ከፍተኛ አቅም ይጠይቃል ነው ያሉት።

ጤና ሚኒስቴር አንፃራዊ ሠላም በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ለጤና ተቋማቱ የሕክምና መስጫ ቁሳቁስ በመላክ ስራ ለማስጀመር የሃብት ማሰባሰብና የማሰራጨት ስራ እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አቅም ያላቸውና ጉዳት ያልደረሰባቸው ሆስፒታሎች በአካባቢያቸው የሚገኙ የተጎዱ ጤና ጣቢያዎችን እንዲደግፉ የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እስካሁን በአፋርና በአማራ ክልሎች ጉዳት የደረሰባቸውን 20 የጤና ተቋማት ዳግም ስራ ለማስጀመር ሙሉ የቁሳቁስ ስርጭት መደረጉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በተቋማቱና የሕክምና ቁሳቁስ ላይ ከደረሰው ውድመት በተጨማሪ በርካታ አምቡላንሶች መሰረቃቸውንና በተቀሩት ላይም ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ይህንንም ችግር ለመፍታት ጤና ሚኒስቴር አምቡላንሶችን መላኩን ገልጸዋል ዶክተር ሊያ።

ጉዳት የደረሰባቸውን አምቡላንሶች ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት በተደረገው ጥረት 93 አምቡላንሶች ተጠግነው ወደ ስራ መግባታቸውን፤ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ደግሞ በጥገና ላይ መሆናቸውን አክለዋል።

"አገርን ለማስቀጠልና ወደፊት ለመሄድ ሁሉም በአንድ የሚቆምበት ወቅት ነው" ያሉት ዶክተር ሊያ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት እንደ አዲስ ለማቋቋም ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

እየተካሄደ ባለው የማቋቋም ሂደት ድጋፍ እያደረጉ ላሉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም