የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሀገር ህልውና እና ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቀዳሚ ስራቸው ሊሆን ይገባል

493

ህዳር 9/2014/ኢዜአ/ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሀገር ህልውና እና ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቀዳሚ ስራቸው ሊሆን እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የግል መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ገለጹ፡፡
አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃንና የዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተለይም ስመ-ጥር የሆኑ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ሆነ ብለው መረጃን በማዛባት ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ እየሰሩ ነው፡፡

ታዲያ በዚህን ወሳኝ ወቅት የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሀገር ህልውና እና ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ቀዳሚ ስራቸው ሊሆን እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) ከምስረታው ጀምሮ መቀመጫውን በውጭ ሀገር በማድረግ አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ የዘረጋውን የአፈና እና ጭቆና ስርዓትን ሲታገል ቆይቷል፡፡

ከሶስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎም ኢሳት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዋናነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡

የኢሳት ቴሌቪዥን የዜና ክፍል ኃላፊ አቶ ጌራ ጌታቸው እንደሚሉት፤ ኢሳት አሸባሪው ህወሓት አሁን እያደረሰ ያለውን ጥፋት መነሻ በማድረግ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ ቡድኑ ለኢትዮጵያ እንደማያስፈልግ ሲታገል እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ጣቢያው የአገር ህልውና ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የዜና እና ወቅታዊ ዝግጅቶችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እንደ ኢሳት ሁሉ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ሙሉ ትኩረታቸውን አገር ህልውና መጠበቅ ላይ ማድረግ እንዳለላባቸውም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ለውጡን ተከትሎ ራሱን በአዲስ ስያሜ በማደራጀት የሚዲያ ዘርፉን የተቀላቀለው አዋሽ 90 ነጥብ 7 ኤፍ ኤም ሬዲዮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ህልውና መከበር ትኩረት አድርጎ ከሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

የአዋሽ ኤፍ ኤም ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ሲራ፤  ሰርቶ መኖር የሚቻለው አገር ሲትኖር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አዋሽ ኤፍ ኤም  የግልና ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ቢሆንም ለሀገር ህልውና መጠበቅ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጣቢያው ዝግጅቶች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና  ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ  በበኩላቸው  በኢትዮጵያ ፈቃድ ወስደው  የሚሰሩ የግልም ሆኑ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን  የኢትዮጵያ  ሀብት መሆናቸውን መገንዘብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ መገናኛ ብዙሃን አገርና ህዝብ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ወቅት ዜጎች በጋራ ቆመው አደጋውን እንዲመክቱ ህዝብን ማንቃት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ኀብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ አገርን ለማዳን ለሚደረጉ ጥሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አንስተው፤ በተለይ  አሸባሪው  ህወሓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፅመው  ግፍና መከራ  ለሀገር ውስጥና  ለዓለም አቀፍ  ማህበረሰብ በማጋለጥ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ብሔራዊ ጥቅም ላይ ሁሉም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለስልጣኑ ይህን መሰረት ያደረገ የሞኒተሪንግ ስራ መስራቱን ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ያለችበትን የህልውና ዘመቻና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚመጥን  መልኩ  ዝግጅት ቀርጸው ህዝብን እያነቁ ያሉ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ  ኢሳት ቴሌቪዥን እና አዋሽ 90 ነጥብ 7 ኤፍ ኤም ሬዲዮ እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና ችረዋል።

በተለይም ሁለቱ መገናኛ ብዙሃን ለውጡን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ አዲስ በመደራጀት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡