1439ኛው የኢድ አልድሃ የዓረፋ በዓል ዛሬ በመቀሌ ከተማ የሰማእታት ጎዳና በድምቀት ተከበረ

73
መቀሌ ነሀሴ 15/2010 1439ኛው የኢድ አልድሃ የዓረፋ በዓል ዛሬ በመቀሌ ከተማ የሰማእታት ጎዳና በድምቀት ተከበረ፡፡ የመቀሌ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼክ ዋሃብሩክ ካሕሳይ በዚህ ወቅት እንዳሉት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በእርቀ ሰላም በመፍታት ለሃገራቸው ሰላምና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ መስራት አለባቸው። ''ሙስሊሙ ህብረተሰብ ችግሩን በመመካከር የመፍታት ልምድ ሁሌም አለው'' ያሉት ሼክ ዋሃብሩክ አሁን በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለውን የሰላም እጦት ወደ ነበረበት እንዲመለስ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የመቀሌ ከተማ ከንቲባን ወክለው የተገኙ የመቀሌ ከተማ የመንግስትና ህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሳሃ በበኩላቸው በሃገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት የተገኙ ድሎችን ለመቀልበስ የሚሯራጡ ሃይሎችን ለመመከት መስልሙ ህብረተሰብ ሊረባረብ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የእምነቶችና የሃይማኖት እኩልነትን በማረጋገጥ የህዳሴ ጉዞ የጀመረችው ኢትዮጵያን ከጸረ ሰላም ሃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመጠበቅ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከሌሎች ወድሞቻቸው ጋር በመሆን በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም ያሳስበዋል፡፡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ከድጃ መሐመድ በሰጡት አስተያየት የእስልምና እምነት ተከታዮች ሁሌም ለሰላም የቆሙ በመሆናቸው በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አሁን እየታየ ያለውን ሁከትና ብጥብጥ ወደ ቀደመው ሰላም ለመመለስ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡ ሰላም ከሌለ ልማትና የመኖር ዋስትና ፈጽሞ የለም ያሉት ወይዘሮ ከድጃ ሁሉም ህብረተሰብ ለሰላም መጠበቅ ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የኢድ አልድሃ ዓረፋ በዓል  ምእምናን የሶላት ስነ ስርዓትን በማድረግ አጠናቀዋል።                                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም