የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወታደራዊ ጥበብና ኢንዶክትሬሽን እንዲጎለብት ታላቅ ስራ ሰርተዋል--የሰሜን እዝ አባላት

142
መቀሌ ነሃሴ15/2010 የሃገር መከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ ጥበብና ኢንዶክትሪኔሽን እንዲጎለብት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተጫወቱት ሚና የጎላ እንደነበር በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ገለጹ። ’’ኢትዮጵያና በመለስ የአመራር ጊዜ የተገኙ ትሩፋቶች’’ በሚል ርእስ በኢፊዴሪ የሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ስድስተኛ ዓመት ዝክረ መለስን ምክንያት በማድረግ ትናንት ውይይት አካሂደዋል። በዚሁ ወቅት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የስነልቦና ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ቢነጋ ሃይለ ስላሴ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው የነበራቸውን የአመራር ጥበብና ለአገሪቱ እድገት ያበረከቱት አስተዋፅኦ አስመልክቶ ፅሁፍ አቅርበዋል። ረዳት ፕሮፌሰሩ በዚሁ ጽሁፋቸው እንደገለጡት አገሪቱ በህገመንግስታዊ ስርዓት እንድትመራና የሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች መብት እንዲከበር የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ሙሉ ስብእና እንዲኖረውና ከኢትዮጰያ አልፎ ለአፍሪካ አህጉር ዘብ የቆመ ሰራዊት እንዲሆን የሚያስችል ስትራቴጂ ቀያሽ እንደነበሩ ተናግረዋል። እንዲሁም ''ሰራዊቱ ህዝባዊ ወገንተኝነትን ጠብቆ እንዲራመድ በመቅረፅ የአቶ መለስ ዜናዊ አሻራ የጎላ ሚና ነበረው'' ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ። የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥ ለሎጂስቲክስ ሜጀር ጄነራል አስራት ዳኔሮ  በበኩላቸው ''የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናው ስድስተኛ ዓመት ህልፈት የምንዘክረው አደራቸውን በይበልጥ ለመወጣት ቃላችን በማደስ  ነው'' ብለዋል። አቶ መለስ ሰራዊቱ የሚማርበትና የሚገነባበት፣ ለህገመንግስቱ በታማኝነት የሚያገለግልበትን በርካታ  ጽሁፍ የፃፉና ያስተማሩ መሪ እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡ የሰራዊቱ አመራርና አባላትም የእሳቸውን አደራ ለመወጣት ለአገሪቱ ህገመንግስታዊ ሉአላዊነትና ሰላም መረጋገጥ እንደሚታገሉ ተናግረዋል፡፡ ከሰሜን እዝ አባላት መካከል የሃምሳ አለቃ አይቸው መልካሙ እንደገለፁት አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው የሰራዊቱን አቅም እንዲጎለብት ያበረከቱት አስተዋፅኦ የጎላ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ''አቶ መለስ እንደ መከላከያ ሰራዊት ያስቀመጡዋቸው ግቦች ተከትሎ በመራመድና ለህገመንግስቱ ታማኝ በመሆን ለአገሬ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ።’’ ብለዋል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የብሄሮችና ብሄረሰቦች ተዋፅኦ እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ ሁለንተናዊ ስብእናው ጠንካራ እንዲሆን ሰርተው ማለፋቸው የገለጹት ደግሞ የእዙ አባል የምክትል አስራ አለቃ ቦንቱ አለማየሁ ናቸው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም