በኢትዮጵያ ሀይቆች ላይ እየተስፋፋ የሚገኘውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ ያስፈልጋል

124

ህዳር 7/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሀይቆች ላይ እየተስፋፋ የሚገኘውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በዝዋይ ሀይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም ያለበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአገሪቱ ሀይቆች ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል  ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ ያስፈልጋል።

የእምቦጭ አረም በኢትዮጵያ በሚገኙ ሀይቆች ላይ አደጋ በመደቀኑ ችግሩን ለመከላከል ምሁራንና ህብረተሰቡ በቅንጅት መስራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

እምቦጭን በኬሚካል ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት በአሳ ሃብት ላይ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ በሰው ኃይል ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት አዋጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዝዋይ ሃይቅ በእምቦጭ አረም ምክንያት አደጋ ውስጥ መግባቱን ህዝቡ ተረድቶ በመከላከሉ ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በአገሪቱ በሚገኙ በአብዛኛው ሀይቆች ላይ አረሙ መከሰቱን ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ከጣና ሀይቅ ከ4 ሺህ በላይ ሄክታር እምቦጭ አረምን በማጽዳት ጥሩ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በአገሪቱ ሀይቆች ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የባቱ ከተማ የአካባቢ ክብካቤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ወንድሙ በበኩላቸው በዝዋይ ሀይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሸፈኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ በ80 ሄክታር ላይ የበቀለውን አረም ለመንቀል ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በመተባበር ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

ሀይቁ ለበርካታ ዜጎች የገቢ ምንጭ መሆኑን ገልጸው፤ አረሙን ለማጥፈት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም