በቦሰት ወረዳ ትናንት በደረሰ የኤሌክትሪክ አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት አለፈ

1056

አዳማ ነሃሴ 15/2010 በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ትናንት በደረሰ የኤሌክትሪክ አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በአራት ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ መድረሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት ትናንት ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ በነዋሪዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ የደረሰው በወረዳው ዳንጉሮ ጥዬ ቀበሌ የፈነዳውን የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ተከትሎ የተበጠሰ የኤሌክትሪክ ገመድ በመርገጣቸው ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ችግር ሲያጋጥም  በወቅቱ ለሚመለከተው ክፍል ማሳወቅ እንጅ ወደ አካባቢው መቅረብ ለአደጋ ስለሚያጋልጥ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ ዞን ዱግዳ ወረዳ ደራራ ዶሌቻ ቀበሌ  ለመስኖ ልማት የተቆፈረ ጥልቅ ጉድጓድ ትናንት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ተደርምሶ የሦስት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

ጉድጓዱ 12 ሜትር ጥልቀት ያለው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የውሃ ጉድጓዶች ያሉበት አካባቢ ስለሚርስ ህብረተሰቡ በአካባቢው ሲንቀሳቀስ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ኮማንደር አስቻለው አስገንዝበዋል፡፡