መንግስት በሉዓላዊነት ላይ ያለው የጸና አቋም ምእራባዊያን ጫናቸው እንዲበረታ አድርጓል

እንጅባራ፣ ህዳር 7/2014(ኢዜአ) መንግስት በሉአላዊነት ላይ ያለው የጸና አቋም ምእራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ ጫናቸው እንዲበረታ አድርጓል ሲሉ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ።

ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ምእራባዊያን ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፍረስ  አሸባሪው ህወሀትን እንደ ዋና መሳሪያቸው እየተጠቀሙበት መሆኑን አመልክተዋል።

ምሁራኑ አክለው "በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ያለው ጽናትና ተላላኪነትን ላለማስቀጠል የያዘው ጠንካራ አቋም  ለምዕራባውያን ምቾት አልሰጣቸውም"።

በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህርና ጠበቃ አቶ እንደገና አማረ  መንግሥት ሉዓላዊነትን የሚያስደፍሩና በዘመነ ህወሓት የነበረውን የተላላኪነት ሚና አላስቀጥልም  ማለቱ ምእራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጓቸው ጫናዎች እንዲበረቱ ማድረጉን አመልክተዋል።

ምዕራባዊያኑ በምርጫ ሥልጣን የያዘን መንግሥት የሚነቅፉትና የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙት በቀጣናው የነበራቸውን ጥቅም እናጣለን በሚል ስጋት እንደሆነም አስረድተዋል።

እንደ ምሁሩ ገለጻ ምእራባዊያን ህወሀትን ዳግም ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚያደርጓቸውን ጫናዎች ተቋቁሞ የህልውና ዘመቻውን በድል ማጠናቀቅ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ከቀጠናው አገሮች ጋር የጀመረችውን የሠላም ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ምሁሩ አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና የሥነ-ተግባቦት መምህር ታደለ አምበሉ በበኩላቸው "የውጭ መገናኛ ብዙሀን  የሀሰት ዘገባ ፍብሪካ ላይ የተጠመዱት አሸባሪው  በኢትዮጵያና በዜጎቿ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ ስላልተረዱት አይደለም" ብለዋል።

"ይልቁንስ ምእራባዊያን ህወሀትን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም መቆጣጠሪያ መሣሪያ በማድረጋቸው ስለሆነ ነው " ሲሉ አመልክተዋል።

በአፍሪካ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት"መረጃ ሸቀጥ ነው" በሚል ቀድመው የሀሰት መረጃዎችን እያመነጩ እያሰራጩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ድርጅቶችን መሥራች፣ መቀመጫ እንዲሁም የጥቁሮች የነጻነት ተምሳሌት በመሆኗ ምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀኖቻቸውን በመጠቀም ሀገሪቱን ጥላሸት ለመቀባት የሚሯሯጡበት ሌላው የጫናው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

''በዚህ ምክንያት ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ማዳከም አፍሪካን ማዳከም ነው'' ብለው በማሰባቸው እንደ ግብጽ ያሉ አገሮችን  በመጠቀም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ገንብታ በኢኮኖሚ እንዳትበለፅግ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

ምዕራባዊያን አሸባሪው ህወሀት ሲከተለው የኖረው የፖሊሲ አካሄድ  ፍላጎታቸውን ደጋፊ ሆኖ ስላገኙት ኢትዮጵያን ማፍረሻና ማዳከሚያ መሣሪያቸው እንዳደረጉት መምህር ታደለ አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀንና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ጫናዎቹን ለመመከት አበክራ ልትሰራ እንደሚገባ ምሁሩ አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም