የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩ በወላይታ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ

81
ሶዶ ነሃሴ14/2010 የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ አንድነትን ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በወላይታ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ፡፡ ሰራተኞቹ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከዞኑ አስተዳደር ጋር ተወያይተዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ቆርጋ ላምበቦ እንደተናገሩት የህዝብን መብት  በማስከበር ጤነኛ የሆነ የእርስ በርስ ግንኙነትን ማጠናከር አሁን ላይ በሃገሪቱ የሚስተዋለው ህገ ወጥ ድርጊትን  ለመቆጣጠር የሚበጅ ነው፡፡ ፍትህን በማዛባት በህዝቦች መካከል ችግር እንዳለ በማስመሰል ሁከቶችን ለመፍጠር የሚታትሩ ግለሰቦችን ለማስቆም መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ግዴታውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ አሁን ላይ የመጣው የነጻነት መንፈስ እንዳይቀለበስ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት በመደመር፣ በፍቅር፣ በይቅርታና እኩልነት መርህ ሰላማዊ ትግል የሚያደርጉና ለህዝብ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚችሉ አመራሮችን  በአዲስ ማደራጀት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ "በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል በወጣቱ ምክንያታዊ አስተሳሰብና ስብዕና ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል " ብለዋል፡፡ የአካባቢዉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ አቶ ከበደ አንጁሎ በበኩላቸው  ከወጣቱ ፣ከኃይማኖት መሪዎች፣ ከሃገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ጋር እንደየደረጃቸው የሚመጥኑ የውይይት መድረኮች ሊመቻቹ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ "የውይይት መድረኮቹ  የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል፡፡ የሰላም እጦት በልማት ላይ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት በተለይም ወጣቱ በሰከነ መንፈስ ተስፋውን ሊመለከት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ አንድነትን በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  የበኩላቸውን እንደሚወጡ ሰራተኞቹ ተናግረዋል፡፡ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ፣በሃዋሳና አከባቢዋ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ስለማቋቋም ፣በሲዳማና በወላይታ ብሄረሰቦች መካከል እየተካሄደ ያለው የእርቀ ሠላም ሂደት የደረሰበት ደረጃ በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ተፈናቃይ ወገኖች ወደቀያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን ገልጸው በዘላቂነት ለማቋቋም ከክልሉ መንግስት ጋር በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በሃዋሳና አካባቢዋ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሲዳማና በወላይታ ብሄረሰቦች መካከል እየተከናወነ ያለው የእርቀ ሰላም ሂደት በጠንካራ ጎኑ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ ህዝብን ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአመራር አደረጃጀቱን ምላሽ በሚሰጥና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንደሚዋቀርም አስታውቋል፡፡ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ላይም በትኩረት እንደሚሰራ ነው ዶክተር ጌታሁን ያመለከቱት፡፡ በውይይት መድረኩ ከዞኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም