የጌዲኦ ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

63

ህዳር 5/2014 (ኢዜአ)የጌዲኦ ዞን ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ ደርቤ ጅኖ ድጋፉን ለመከላከያ ህብረት ሎጂስቲክስ መምሪያ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ኮለኔል ሹማ ኦብሳ አስረክበዋል።

በዞኑ ከተደረገው ድጋፍ 7 ሚሊዮኑ በገንዘብ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በአይነት መሆኑንም በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።

በአይነት ከተደረገው ድጋፍ 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 172 ሰንጋዎች፣ 114 በጎች እንዲሁም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የስንቅ ዝግጅት መሆኑን ተናግረዋል።

ከአይነትና ገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ የዞኑ አመራሮች የሽብር  ቡድኑን ለመደምሰስ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን መሰለፋቸውንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በቀጣይም በዱር በገደል አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እየተዋደቀ ላለው ሰራዊት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የመከላከያ ህብረት ሎጅስቲክስ መምሪያ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ኮለኔል ሹማ ኦብሳ፤ የጌዲኦ ዞን ነዋሪዎች የህልውና ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ መሰል ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁንም ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት አሸባሪውን ህወሃት በተለያዩ አውደ ግንባሮች እየተፋለመው ሲሆን መላው ህዝብም ለሰራዊቱ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም