የአሸባሪውን እኩይ ተግባር ለመከላከል የፖሊስ አባላት ድርሻ ከፍተኛ ነው

199

ሀዋሳ ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) የፖሊስ አባላት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ህወሓት በተላላኪዎቹ አማካይነት በየአካባቢው ሁከት ለመፍጠር የሚያደርገውን እኩይ ተግባር የማምከን ኃላፊነታቸውን በትጋት መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

በደቡብ ፓሊስ ኮሌጅ የከፍተኛና መካከለኛ የፖሊስ አመራሮች የማዕረግ ሽግግር ሥልጠና ሲወስዱ የቆዪ የደቡብና የሲዳማ ክልሎች የፖሊስ አባላትን አስመርቋል ፡፡

ኮሌጁ ከፍተኛ አመራሮችን ለ9ኛ ዙር መካከለኛ አመራሮችን ደግሞ ለ6ኛ ዙር ትናንት ያስመረቀ ሲሆን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የደቡብና የሲዳማ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ፡፡

የደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ህወሓት በውስጥ ከተላላኪዎቹና የብልፅግና ጉዞዋ ሥጋት ከፈጠረባቸው የውጭ ግብረ አበሮቹ ጋር በማበር በከፈተባት የተቀናጀ ጦርነት በከፍተኛ ትግል  ውስጥ ትገኛለች፡፡

አደጋውን ለመቀልበስና ህልውናዋን ለመጠበቅ ጀግኖች ልጆቿ በግንባር እየተዋደቁ ይገኛሉ፡፡

“መተኪያ የሌላት የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያን ዋጋ ከፍለን የመታደግ ኃላፊነት የሁላችንም ነው” ብለዋል።

“በተለይ የፖሊስ አባላት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ዕውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው አሸባሪው ህወሓት በተላላኪዎቹ አማካይነት በየአካባቢው ሁከት ለመፍጠር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የማምከን ኃላፊነታቸውን በትጋት ሊወጡ ይገባል ” ሲሉ  አስገንዝበዋል ፡፡

በማንኛውም ወቅት የሚቀርብላቸውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር በመዝመት ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ለመታደግ ዝግጁ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው ህወሓት በሥልጣን ዘመኑ ሕዝብን ከሕዝብ ለይቶ ደም ሲያቃባ ከመቆየቱ ባለፈ በሠራዊት አባላት ውስጥ ዘረኝነትን በመንዛት ሲከፋፍል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

“ከፋፋይ የሆነ የህወሓት ሴራ አሁን ላይ መክኗል” ያሉት ኃላፊው የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ ከየአካባቢ የተመሙ ጀግኖች በአንድነትና በፅናት እየተዋደቁ መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ፈተና ልክ እንደጥንቱ በልጆቿ አንድነትና ፅናት እንደምታሸንፍ ገልፀው “ይህን ለማረጋገጥ በማንኛውም ግዳጅ ላይ በቆራጥነት ለመሰለፍ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል” ብለዋል ፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል ዕጩ መኮንን ተሰማ ታደሰ እንዳሉት በሥልጠናው ከአካላዊ ዝግጅት ባለፈ ወቅቱ የሚመጥነውን ፖሊሳዊ አመራር መስጠት የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ቀስመዋል።

ከስልጠናው ባገኘሁት ዕውቀት ክህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሠላም ከማረጋገጥ ባሻገር በማንኛውም ጊዜ ከመንግስት የሚተላለፍልትን ጥሪ ተቀብሎ ለሀገሩ በግንባር ለመሰለፍ ዝግጁ ነኝ ብሏል ፡፡

“ኅብረተሰቡ ፀጉረ ልውጦችንና ያልተለመዱ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው” ያሉት ዕጩ መኮንን ዳና አባተ በበኩላቸው በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተግባር ላይ በማዋል የዜጎችን ሠላምና ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከአሁን በፊት የልዩ ኃይል ጓዶቻቸው በሁለት ዙር ወደ ግንባር መዝመታቸውን የተናገሩት ዕጩ መኮንኑ “በቀጣይ ዙር ዕድሉ ከደረሰኝ ወደ ግንባር ሄጄ ለመፋለም ተዘጋጅቻለሁ” ብለዋል ፡፡

ተመራቂዎቹ የፖሊስ አገልግሎትና ሥነምግባር ፣ የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ አመራርነት እንዲሁም የአካል ብቃትና ሌሎች ሥልጠናዎችን ወስደዋል ፡፡