የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እየተደረገ ላለው ዘመቻ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል

266

ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እየተደረገ ላለው ዘመቻ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ሲሉ የስፖርት ቤተሰቦች ገለጹ።

የስፖርት ማህበረሰቡ በሚናፈሱ ወሬዎች ሳይደናገር የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ ቀርበዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በከተማዋ ካሉ የስፖርት ቤተሰቦች ጋር ”በመረረ ትግላችን ጣፋጭ ድል እናጣጥማለን” በሚል መርህ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክሯል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እየተደረገ ላለው ዘመቻ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከአዲስ አበባ የአካል ብቃት አሰልጣኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት አለባቸው፤ ኢትዮጵያን ለማዳን እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ ሁላችንም የጋራ ዓላማ ሰንቀን እየሰራን ነው ብለዋል።

የማስ ስፖርት አሰልጣኙ ወጣት ጌታቸው አሰፋ፤ ለህልውና ዘመቻው ህዝባዊ ንቅናቄ ማካሄድ ወሳኝ በመሆኑ ማህበረሱን በአግባቡ ማንቃት ያስፈልጋል ብሏል።

የአዲስ አበባ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ካሱ አለማየሁ፤ ጠላትን ለመመከት ገንባር መዝመቱ እንዳለ ሆኖ ሁላችንም በየተሰማራንበት የሙያ መስክ ቁርጠኛ ሆነም መስራትም ይገባል ብለዋል።

በተለይም ወጣቶችን ማንቃት፣ ተሳትፏቸውን ማጎልበት እንዲሁም ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደረግን ማንኛውንም ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

የከተሞቸን ሰላምና ፀጥታ ለመቆጣጠር በጋራ መስራት ይገባል ያሉት አቶ ካሱ በአዲስ አበባ ከምሽት መዝናኛ ቤቶች ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለብን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብረሃም ታደሰ፤ የስፖርት ቤተሰቡ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው አሁንም በህልውና ዘመቻው እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ስፖርታዊ ንቅናቄዎችን በስፋት በመተግበር መከላከያ ሰራዊቱን ማበረታታትና ማጀገን ላይ ከአካባቢ እሰከ ግንባር ድረስ እንቅስቃሴ ማድረግ በትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት ይሆናሉ ነው ያሉት።

በውይይቱ ላይ ከ3 ሺህ በላይ የስፖርት ቤተሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።