የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ ለህልውና ዘመቻው 9 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ድጋፍ አደረገ

290

እንጅባራ ህዳር 5/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ በህልውና ዘመቻው እየተፋለሙ ላሉ ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለሌሎች የጸጥታ ሃይሎች 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት የእርድ እንስሳት ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው ለኢዜአ እንዳስታወቁት የዞኑ ሕዝብ ድጋፉን ያደረገው በተለያዩ ግንባሮች ለተሰማሩት መከላከያ ሠራዊት፣የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖዎች ነው።

ድጋፉ 203 ሠንጋዎች፣ 553 ፍየሎችና በጎችን ያካተተ መሆኑን  ገልጸዋል።

ድጋፉ የተሰባሰበው ከወረዳዎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከአገው ፈረሰኞች ማህበርና ከህብረተሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ አሸባሪው ህወሃት እስከሚደመሰስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር ሊቀመንበር አለቃ ጥላዬ አየነው ማህበራቸው የአገር ህልውና በማስከበር ላይ ለሚገኙት የጸጥታ ሃይሎች 120 በጎች መለገሱን ተናግረዋል።

“አገር በጠላትና በከሀዲው ቡድን ሲወረር ዝምታን የሚመርጥ አባል የለም” ያሉት ሰብሳቢው የማህበሩ አባላት ዘመቻውን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ቀደም ሲል ለህልውና ዘመቻው  ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከዞኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።