አብሮነትን የሚንዱ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት

79
አዲስ አበባ ነሃሴ 14/2010 በኢትዮጵያ አብሮነትን የሚንዱ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣ ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዋቂ ግለሰቦች ጠየቁ። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን ለውጥ የሚያደናቅፍ ግብረ-ገብነት የጎደለው እንቅስቃሴ እየታየ ነው ብለዋል። አገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥልና ኢትዮጵያዊ ባህል ያልሆኑ ድርጊቶችን ለማስቆም መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጎን ለጎን የወጣቱን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄ መመለስና ግብረ-ገብነትን በዘላቂነት ማስተማር ይገባል ብለዋል። አርቲስት ደበበ እሸቱ እንዳለው በአሁኑ ወቅት የሚታዩት ግጭቶች፣ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀልና በመንግስት ንብረቶች ላይ ጉዳት ማድረስ ትውልዱን ታሪካዊ ተወቃሽ ያደርገዋል። ወጣቱ ትውልድ መከባበርንና መፈቃቀርን በማጎልበት ከጥፋቶች በመራቅ አርአያ በሆኑ ተግባራት ላይ መሳተፍ አለበት ብሏል። "ወጣቱ መንቃት አለበት ፤ የሚቃጠለው ማንኛውም ነገር የራሱ ሀብት ነው፣ የሚጠፋው ንብረት የራሱ ንብረት ነው፣ የሚነደው አካባቢ የራሱ አካባቢ ነው ይሄን ካለማወቅ ወይም ግንዛቤ ከማጣት አለበለዚያ ደግሞ በእልህና በቁጭት በግብታዊነት ተነስቶ የሚያደርገው ነውና ወጣቱ እርስ በርሱ እየተመካከረ ከጥፋት መሸሽን አርአያ አድርጎ መነሳት አለበት” ተዋናይ ይገረም ደጀኔ በበኩሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዳር ድንበሩ ሲደፈር በአንድነት እንደሚዘምተው ሁሉ አንድነቱና አብሮነቱን የሚሸረሽሩ ተግባራትን መጠየፍ አለበት ብሏል። የህዝብ አብሮነት የሚሸረሽሩ ግጭቶች የአገሪቱን አንድነት ለማይፈልጉ ወገኖች መጠቀሚያ እንዳይሆን መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበር ሥራ መሥራት እንዳለበት አሳስቧል።  “ህግ አለ፤ የህግ የበላይነትም መኖር አለበት ብዬ አስባለሁ ስለዚህ ወደ እነዛ ነገሮች የምንሄድባቸውን ነገሮች መኖር አለባቸው አለበለዚያ በክፍተቶች የሚጠቀሙ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ የምንፈጥራቸው ክፍተቶችና ስህተቶች በኋላ የማይመለሱ ነገሮች ሊያመጡ ይችላሉና በምናደርጋቸው ነገሮች ማስተዋልና እርጋታ መኖር አለበት አንዳንዴ ከስሜታዊነት በተቻለ መጠን መፅዳት አለብን አለበለዚያ የምናደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች ነገ እኛን መልሰው ዋጋ ያስከፍሉናል ስለዚህ ጥንቃቄ ያስፈልጋል” ፖለቲከኛ ዶክተር ካሳ ከበደ በበኩላቸው ወጣቶች ጊዜያቸውን ለአገር በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ እንዲያውሉ ወላጆች፣ ቤተሰቦችና የአካባቢው ማህበረሰብ የመምከርና ጉዳቶችን የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው ብለዋል። የወጣቶችን የሥራ አጥነትና የኢኮኖሚ ጥያቄ ለመመለስ መንግስት ወጣቱን በምርታማነት ተግባራት ላይ ሊያሰማራ ይገባል ነው ያሉት።  “ይሄንን እምቅ የወጣት ኃይል ገንቢ ለሆነ ተግባር ማዋል የሚቻለው እንዴት ነው ሥራ አጥነት አንድ ትልቅ ችግር ነው፣ ኢኮኖሚውን በሚመለከት ረገድ ብዙ የግንባታ ሥራዎች አይቻለሁ በሌላ በኩል ደግሞ የገቢ አለመመጣጠን ስላለ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ  ክፍል የኢኮኖሚ ጫና እንዳለበት በግልፅ ይታያል እና ያ ሊፈታ የሚችለው ይሄንን ወጣት ኃይል በምርትና እና በምርታማነት ተግባራት ላይ በማዋል ይመስለኛል” አርቲስት ሰርፀ ፍሬስብሃት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ከኢትዮጵያዊ እሴቶች ያፈነገጡ ችግሮች መነሻቸው የግብረ-ገብነት ትምህርት ካለመኖር ጋር የተያያዘ ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና አብሮነትን ለማጎልበት የግብረ-ገብነት አስተምህሮት በትምህርት ተቋማት መሰጠት አለበት ብሏል። "መልካም በጎና እውነት የምንላቸው ነገሮች ስነ ውበታዊ ብቻ አይደሉም የሞራልና የግብረ ገብ ጉዳዮች ጭምርም ናቸው። በኛ ህይወት ውስጥ ደግሞ ትልቁ እየጎደለን የመጣው በተለይ ከ1970ዎቹ ከመጣው ካሪክለም ወዲህ ግብረ ገብ የሚባለውን ትምህርት ከትምህርት ስርዓታችን አስወግደን ቁጭ ብለን ነው ያለነው አሁን  ለተፈጠሩት የሞራል ቀውሶች የባህል ትህትና የማጣታችን ችግር መንስኤው ችግር ቢጠና የግብረ ገብነት ትምህርት ካለመኖር ጋር ይያያዛል” የእምነት ተቋማት ግብረ-ገብነትና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በስፋት ሊገፉበት እንደሚገባ ገልጿል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት እንደሚገድቡና መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም