ለ4 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል ፈተና በስኬት ተጠናቋል

131

ህዳር 2/2014 (ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ ለተከታታይ አራት ቀናት ሲሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል ፈተና በስኬት መጠናቀቁን አገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ የፈተናውን መጠናቀቅ በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም 617 ሺህ 991 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከተመዘገቡት ተማሪዎች መካከልም 565 ሺህ 255 ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች 545 ሺህ 381 ተማሪዎች የዘንድሮውን የ12ኛ ከፍል ፈተና የወሰዱ መሆናቸውን  ገልጸዋል።

ፈተናው በተሰጠባቸው 2 ሺ 36 የፈተና ጣቢያዎች በስኬት መጠናቀቁንም ጠቁመዋል፡፡  

አገሪቷ በውስጥ እና በውጪ እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት ፈተናው በስኬት መጠናቀቁ ትልቅ ድል ሆኖ መወሰድ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

ይህም ወደ ፊት ሌሎች ልማቶችን ለማረጋገጥ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፈተናው ሂደት አንዳንድ ችግሮች መግጠማቸውን ገልጸው ወዲያው መፈታት የነበረባቸው ተፈተው በተሻለ ሁኔታ ፈተናው መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ ፈተናው ወጥቷል የሚል ጥቆማ እንደደረሳቸው የገለጹት ሃላፊው ይህም በቀጣይ ታይቶ በማስረጃ የሚረጋገጥ ከሆነ እርምጃ ወይም ማስተካከያ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።  

በማስረጃ ተረጋግጦ ትክክል ከሆነ በትምህርት ቤት ደረጃ፣ በተማሪ እና በትምህርት ዓይነት ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ፈተናው ባልተሰጠባቸው አከባቢዎችም ክልሎች ተማሪዎችን ማስፈተን በሚችሉበት ጊዜ ፈተና የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሁን ፈተና የወሰዱት እና በቀጣይ ሁኔታዎች ሲስተካከሉ ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎችም በጋራ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚገቡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለፈተናው ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላደረጉ ተማሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የትምህርት ማህበረሰብ እና በየአከባባው ለሚገኙ አመራሮች ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም