“በእሳት ላንቃ እንደተጣለ ገለባ ተቃጥሎ እያለቀ ነው”

353

“…በእሳት ላንቃ እንደተጣለ ገለባ ተቃጥሎ እያለቀ ነው።”

እንግዳው ከፍያለው (ከባህር ዳር ኢዜአ)

አሸባሪው ህወሓት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ጥሏቸው የሄደው እንቁላሎች አሁን ላይ የተፈለፈሉ ቢመስሉም ከጫጩትነት አልፈው ክንፍ በማውጣት እንደፈለጉ በመብረርና ጥቅም ላይ መዋል አልቻሉም።

የፌደራሊስት ሃይሎች ብሎ ለማሰባሰብ የሞከራቸው ድርጅቶችም የአሸባሪው አገር የማፍረስ ሴራ ሲገባቸው “ጨዋታው ፈረሰ፤ ዳቦው ተቆረሰ” ብለው ሸሹት።

ህወሓት የበግ ጸጉር የለበሰ ተኩላ መሆኑን ሲረዱ ሁሉም “መንገዱን ጨርቅ ያርግልህ” ብለው አውግዘው ተለዩት። በርግጥ ከተጣሉት እንቁላሎች ውስጥ እንደ ሸኔ አይነቶቹ ክንፍ አውጥተው ለመብረር አቅም ቢያንሳቸውም እስካሁን ድረስ አለንልህ፤ ከጎንህ ነን…ብለው መጨፈራቸው አልቀረም።

የእዚህ ሁሉ ሴራ ምንጭ የሆነው የአሸባሪው ህወሓት ዋና አላማና ግብ ኢትዮጵያን ማፈራረስ መሆኑን የራሱ ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጧል። ለእዚህም ሲኦል ድረስ ከመግባት ወደ ኋላ እንደማይሉም በአደባባይ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሀት የቋንቋ ፌደራሊዝም ስርዓት በመገንባት በሂደት አገር ለማፍረስ ቢያልምም በስነልቦና የተግባባው መላው ኢትዮጵያዊ ሆ ብሎ በመውጣት ህልሙን ፉርሽ አደረገበት። አሁን ላይ የመጨረሻ ሙከራውን ለማስፈጸም ላይ ታች እያለ ያለው በረብጣ ዶላር የገዛቸው ቅጥረኞችና ዲጅታል ወያኔዎች በመጠቀም ብቻ ነው።

አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት፣ መንግስታትና ድርጅቶች ለሽብርተኛው ህወሀት በተለያየ መንገድ ውግንናቸውን ሲያሳዩም ተስተውሏል። እነዚህ አካላት አሸባሪው በገዛቸው አሸማጋዮች (ሎቢስቶች) ስር ተጠልፈው አሸባሪውን ቡድን ደግፈው በመታገል ላይ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለዚህ አንዱ ማሳያ ድሃ ብለው አፋቸውን ሞልተው የፈረጇት ኢትዮጵያ ላይ ያለ እረፍት ከ10 ጊዜ በላይ በጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆና እንድትቀርብ መጣራቸው ነው።

ምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀኖቻቸው በቀናት ውስጥ ለ70 ጊዜ አፍራሽ ዘገባ የሰሩባት አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት። የአድዋ ድል ባለጸጋዋንና የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውጭ ሃይሎች አሸባሪው ህወሓትንና ተላላኪዎቹን በመጋለብ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩ ሉአላዊነትና ጸንቶ ለኖረው ክብሩ ያለውን ጽኑ እምነት በተደጋጋሚና በተለያየ ጊዜ ቢያስመሰክርም አይናቸውን በጨው አጥበው አላየንም፣ አልሰማንም…ካሉ ሰነባብተዋል። ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ የአሸባሪው ህወሓትን ወደ ስልጣን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ለዚህ በሙሉ አቅማቸው ደግፈው አብረው ይውተረተራሉ።

ከወልድያ ጀምሮ በአንዳንድ የውጊያ ግንባሮች የውጭ ተዋጊ ሃይሎች ከአሸባሪ ጋር ተሰልፈው እየተዋጉ ምርኮኛ፣ ሙትና ቁስለኛ ሆነው የተገኙትም ለዚሁ ዓላማቸው ሲባል ነው።

ምዕራባውያን አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍና በደል እንኳን ዳግም ወደ ስልጣን ለመምጣት ይቅርና እዚች ምድር ላይ መኖር እንደማይገባው ጠፍቷቸው አይደለም። ነገር ግን በከፋፍለህ ግዛው መርህ የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በእርስ በማጫረስ ለመበታተን የወጠኑት የቆየ ፕሮጀክት ግብ ሳይመታ የአሸባሪው ህወሀት መወገድ የፈጠረባቸው ቁጭት ነው አሁን ላይ ኢትዮጵያ ላይ ይፋዊ ዘመቻ ያስከፈታቸው።

በወቅታዊና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ይሄንኑ ጉዳይ አብራርተዋል። የትግራይ ወራሪ ሃይል የወረሰው የባንዳነት ባህሪ፣ ሌላውን ህብረተሰብ ዘርፎና ገዝቶ ፍላጎቱን ማሟላት ጥርሱን የነቀለበት ተግባሩ ነው። የእዚህም መነሻው ከበታችነት የመነጨ ምኞት መሆኑን ነው የገለጹት። ይህን ምኞት ነው ህዝብን ጨቁኖ መኖሩ ሳይበቃው ለወደፊትም የባርነት ቀንበር ለመጫን እየተፍጨረጨረ ያለው።

አሸባሪው ህወሀት ቀቢጸ ተስፋውን ይዞ ዋነኛ ጠላት፣ ደመኛና ከስልጣን ያገለለኝ የአማራ ህዝብ ነው ብሎ በመፈረጅ በሒሳብ እናወራርዳለን ስሌት ህዝቡን ለማጥቃትና ለመዝረፍ አማራንና አፋርን የወረረው።

ህወሓት በየጊዜው ወረራ ቢያካሂድም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ታላቅ የእሳት ላንቃ እንደሚጣል ገለባ ተቃጥሎ ማለቁ የማይቀር መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። አሸባሪው የትግራይን ታዳጊ ህጻናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን ጭምር በአማራ ተራሮችና ሸለቆዎች ላይ እያሰማራ ይገኛል። አሁን ላይ የአማራን ህዝብ ከመተንኮስ አልፎ ትእግስቱንና የአብሮነት ስሜቱን እየተፈታተነው ነው።

በእዚህም የህዝቡ ትዕግስት ከልክ በላይ በመሆኑ አሸባሪው እስከወዲያኛው በጠላትነት እንዳይገዳደረው ለማድረግና ህልሙንም ሳያሳካ ለመደምሰስ ቆርጦ ተነስቷል። ከክልሉ ህዝብ በተጨማሪ መላው ኢትዮጵያዊያን ትብብራቸውን በቁርጠኝነት እያሳዩ እንደሆነ ነው አቶ ግርማ የገለጹት።

እሳቸው እንዳሉ የአማራ ህዝብ ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር በመልካም አብሮነት መኖር ብሎም አገርን መገንባት የሚችል ነው። ይህንንም ለዘመናት በተጨባጭ አሳይቷል። እስካሁን የአማራ ህዝብ ጠላቶችና ተላላኪዎቹ በውስጡ አብረውት እየኖሩና ነገር እያሴሩበት በትዕግስት ሲያሳልፍ መቆየቱን ነው አቶ ግርማ ያስታውሳሉ።

የአሸባሪው ዓላማና ተልዕኮ በግልጽ ስለታወቀ ከእስካሁኑ ለየት ባለ መንገድ መላው ህዝብ አቅሞቹን ሁሉ አሰባስቦ ቡድኑን ለመደምሰስ እየተመመ ነው። የክልሉ መንግስት የክተት ጥሪ ያቀረበውም ጉዳዩ አንገብጋቢና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ነው።

“አሁን ላይ እያየን ያለነው የአማራ ተራሮች ከአሸባሪው ታጣቂዎች መፈንጫነታቸው አልቆ  ደም መፍሰሻ መሆናቸውን ነው፣ ለክተት ጥሪው ከህዝብ እየተሰጠ ያለው ምላሽ ደግሞ ጠላትን እስከ ወዲያኛው መደምሰስ የሚያስችል ነው ብሎ ከወዲሁ መተንበይ ያስችላል” ብለዋል አቶ ግርማ ።

አቶ ግርማ አክለው “ህዝቡ ከየቤቱ ተነቃንቆ እየወጣ ነው፤ አቅም ያለው ሲዘምት ደከም ያለው ደግሞ ደጀንነቱን በተለያየ መንገድ እያሳየ ነው፤ ባለሀብቱም ሰርቶ ማትረፍ የሚቻለው ሀገር ሲኖር ነው በማለት ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ስንቅ ሲያዘጋጅና ሲዘምት እየታየና እየተሰማ ነው” ብለዋል።

በዚህ መልክ እየተፈጠረ ባለው የህዝብ ማዕበል አሸባሪው ህወሓት እስከ ወዲያኛው መደምሰሱ አይቀርም። የክተት ጥሪው በዋናናት ጠላትን በገባበት ሳይመለስ ቀብሮ የህዝብና የሀገር ህልውናን ማስቀጠል ነው። በክተት ጥሪው ለዘመቻ የተዘጋጀው ሀይል እንዴት ይመራል የሚለው ጉዳይ ትኩረትን የሚጠይቅ ነው። ከህዝቡና ከዘርፉ ጠበብቶች ጋር በመመካከር የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባል። በእዚህ በኩል ክልሉ ተገቢ ትኩረት በመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራበት መሆኑን ነው አቶ ግርማ ያመለከቱት።

እሳቸው እንደሚሉት በህዝቡ ውስጥ አሻባሪውን ሀይል ለመደምሰስ ያለው እልህ፣ ቁጭትና ስሜት ከፍተኛ ነው። ምንም እንኳ ጦርነት አውዳሚ ቢሆንም የአማራ ክልል ህዝብም ሆነ መንግስት ወደ ጦርነት የገቡት ተገደው ነው። ክልሉና ህዝቡ ለሰላም ትኩረትና ቅድሚያ እንደሚሰጥ በተለያዩ ጊዜያት በተጨባጭ አስመስክሯል።

አቶ ግርማ በማሳያነት ሲገልጹ  “በእያንዳንዷ ጊዜ ስለሰላም ዘምረን ችግሮቻችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነበር። ነገር ግን የሰላም ዋጋው ውድ መሆኑን አይተናል።” በማለት ነው። በአሁኑ ወቅት ለሰላም የሚከፈለውን ሁሉ ውድ ዋጋ በመክፈል የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥና ሀገርን ከአፍራሽ ሀይሎች ሴራ ለመታደግ የክልሉ መንግስት የክተት ጥሪ አቅርቧል። ህዝቡ ለጥሪው እየሳየ ያለው መነሳሳትም ይበል የሚያሰኝ ነው።

አቶ ግርማ እንዳሉት ዘመቻውን ውጤታማ ለማድረግ ህዝቡን በየአካባቢው  የማወያየት ሥራ ተሰርቷል። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተካሄደው ጥሪም በህብረተሰቡ ዘንድ መነሳሳትን ፈጥሯል። በተካሄዱ የውይይት መድረኮችም ህዝቡ “ህይወታችንንና ሁሉነገራችንን ገብረን ሰላማችንን እንገዛለን” በሚል ሰላሙን ለማግኘት ቆርጦ መነሳቱን አስተጋብቷል። ለዚህም የጦር መሳሪያ ያለው ብቻ ሳይሆን ትግሉን ሊደግፉ የሚችሉ ባህላዊ መሳሪያዎችን ጭምር ይዞ ህብረተሰቡ ከቀበሌ ወደ ወረዳ ዋና ከተማ፤ ከዚያም ወደ ግንባር መትመም ጀምሯል።

ይህ በግንባር የተሰለፈ ሃይል በተደራጀ አግባብ ሊመራ የሚችልበትን ስልትና አደረጃጀት መቀየስ ደግሞ ሌላው ትኩረት የተደረገበት ጉዳይ ነው። እንግዲህ ህዝቡ በየአካባቢው ለጥሪው በጎ ምላሽ መስጠት ጀምራል፣ እየሰጠም ነው። ድል የሚገኝበትን አቅጣጫ አስቀምጦ ትግሉን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት ደግሞ ለሚመለከታቸው አካላት የሚተው ጉዳይ ነው።

አቶ ግርማ እንዳሉት የአሁኑ የክተት ጥሪ ቀደም ካሉት ዘመቻዎች ለየት የሚያደርገው በየደረጃው ያለው አመራር ከፊት ሆኖ መዝመቱ ነው። ህዝብ ከማስተባበርና በአግባቡ ከማደራጀት ጀምሮ ራሱ ተሳታፊ በመሆን ጥብቅ አመራር ይሰጣል። በትግሉ ማን ምን ይሰራል የሚለው በአግባቡ ተለይቶና ስንቅም በአግባቡ ተዘጋጅቶ የሚመራ መሆኑም እንዲሁ።

“ጦርነቱ የሚካሄደው ለ60 ዓመታት አድፍጦ በሴራና በቂም በቀል ሲዘጋጅ በኖረ የጥፋት ሃይል እና ሀገር በመገንባት፣ ለሰላም በመዘመር፣ ለአንድነት ሲል በኖረና ህሊናውን ባልሸጠ ህዝብ መካከል ነው” ያሉት አቶ ግርማ፣ አሸባሪ ቡድኑ ሀገር በበላይነት እየመራ በኖረባቸው ዓመታት የህዝቡን እንድነት በማፈራረስ ሴራውን ለመፈጸም ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን አመልክተዋል።

ህወሀት በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በሌሎች መንገዶች ህዝብን እየከፋፈለ ለማዳከም ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ጦርነቱ ከእዚህ ሴረኛ ጋር የሚካሄድ መሆኑ ከባድ ቢያደርገውም በስተመጨረሻ ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ማሸነፉ አይቀርም። ለእዚህ ደግሞ ከዚህ ሃይል ጋር የሚካሄደው ጦርነት ባጭር ጊዜ ግን ደግሞ በተሟላ ዝግጅት መከናወን ይኖርበታል።

ሀገር የማፈራረስ ዓላማ ይዞ የተነሳውን አሸባሪ ህወሓት ከነተላላኪዎቹ ለማጥፋት ህዝቡ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ህዝቡ ቆርጦ ተነስቷል። በእዚህም ጠላትን ድል አድርጎ ህልውናው የሆነውን  ሀገርን መታደጉ የማይቀር ነው።

“አሸባሪ ህወሓት በፖለቲካ ስልጣን ላይ በቆየበቻው ዘመናት “ከጦርነት ወደ ልማት” በሚል ሰበብ የክልሉን ህዝብ መሳሪያ ቀምቶታል” ያሉት አቶ ግርማ መሳሪያ ማስመለስ ድል ለማግኘት ቀዳሚና አስፈላጊ ነው። ህዝቡ በትጥቅ የነበሩበት ክፍተቶች አሁን ላይ እየተሟሉ በመሆኑ በጽኑ አደረጃጀት ወደ ትግል ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

“አሸባሪውን በገባበት ገብቶ ለመደምሰስ የስነ ልቦናና አካል ብቃት እንዲሁም የወታደራዊ ሳይንስ፤ እውቀትና የግብአት አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ማንም ሰው መገመት አያቅተውም “ያሉት  አቶ ግርማ በእዚህ ረገድ ክልሉ ተገቢ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

“ያለፈው አንድ ዓመት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጠላት ዓላማውን ለማስፈጸም ፊት ለፊት ጦርነት መግጠምን ብቻ አይደለም የመረጠው፤ በተለያየ መንገድ ለድል ያበቃኛል ያለውን ተንኮልና ሴራ ሁሉ ቀድሞ አስቦበት ሲፈጽም ቆይቷል፤ አብረውን የኖሩና ጤናማ ግንኙነት አለን ብለን ያሰብናቸው ባንዳዎችንም ለዚህ ሴረኛ ሃይል ቅጥረኛ ሆነው እየሰሩ ነው” ያሉት አቶ ግርማ በቅርቡ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የሆነውን በማሳያነት ጠቅሰዋል ።

አሸባሪው የሚሰራው ደባ እየተደጋገመና እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አሁን በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ተፈጥሯል ያሉት አቶ ግርማ  መረጃ ለጠላት የሚያቀብሉና የባንዳነት ስራ በሚፈጽሙን በህዝብ ትብብር በመለየት በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

“ችግሩን ለመከላከል በዋናነት ህብረተሰቡ በሰፈርና በአካካቢ አደረጃጀት ውስጡን ማጥራት ይኖርበታል። ተግባሩም በእጅጉ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ አመራሩም ህዝቡን የማንቃት ስራ መስራት ይኖርበታል። የውስጥ ባንዳዎችን የመለየቱ ስራ “ሁሉንም አናምንም፤ ሁሉንም አንጠራጠርም” በሚል መመራት ይኖርበታል” ብለዋል።

“እስካሁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ በቡድንና በተናጠል የአሸባሪውን ህወሓት ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ በጥርጣሬ የተያዙ አሉ፤ የተጀመረውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ በማስቀጠል የሰርጎ ገቦችና የባንዳዎችን እንቅስቃሴ ለማስቆም በትብብርና በቅንጅት መስራት የግድ የሚልበት ጊዜ ነው”  ሲሉም አመልክተዋል።

አቶ ግርማ እንዳሉት ዛሬ በተለይ የአማራና አፋር ህዝብ እንዲሁም ሀገር ችግር ውስጥ ብትሆንም ሁሉም ነገር መስተካከሉ አይቀርም። በበጎም በመጥፎም የሰራናቸውም በታሪክ ማህደር መስፈራቸው እንዲሁ  የሚቀር አይደለም። በመሆኑም ለአሸባሪው መረጃና ስንቅ የሚያቀብሉ፣ በገንዘብ የሚደግፉ፣ ወገንን ከኋላ ሆነው የሚወጉና ሌሎች ሻጥሮችን የሚሰሩ አካላት ከእኩይ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል። መላው ህዝብም በክተት ጥሪው ወደ ግንባር ከመዝመት ባሻገር በጉያው ተሰግስገው ያሉ ከሃዲዎችን እያሰሰ ለህግ አካላት ማቅረቡን ሊያጠናክር ይገባል።

“አሁን እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ የተደቀነውን አደጋ በመቀልበስ የአሸባሪውን ህወሓት ግብአተ መሬት ከመፈጸም የበለጠ አጀንዳ የለም፤ ቡድኑን መደምሰስ ለተወሰነ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያንን ተሳትፎ ይጠይቃል፣ በመሆኑም እንደ ሀገር የተጀመረው ርብርብና አንድነት ሊጠናከር ይገባል” ብለዋል ።

አቶ ግርማ በማያያዝ “ሁላችንም ሀገር ከእኔ ምን ትጠብቃለች በሚል የድርሻችንን ከተወጣን የኢትዮጵያችን ድካም ይቀንሳል፣ ለህልውና ሲባል ምንም የምንቀንሰውና የምንሰስተው ነገር ሊኖር አይገባም፣ ያኔ ነው ድል ማግኘትና ማጣጣም የሚቻለው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የተሰለፍነው ለዓመታት የተሰራብንን የመከፋፈል ሴራና የውጭና የውስጥ ጠላቶችን ሴራ ምስጢሩ ስለገባን ነው ሲሉም ተናግረዋል።