ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የኢድ አል አደሃ አረፋ በዓልን በማስመልከት የመልካም ምኞት መልእክት አስተላለፉ

118
አዲስ አበባ ነሃሴ 14/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለ1439ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢድ አልአደሃ (አረፋ) በዓልን በማስመልከት የመልካም ምኞት መልእክት አስተላለፉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፆም፣ በፀሎትና ክፉ ምግባርን በመኮነን የሚከናወነው የአረፋና የሐጅ ስርዓት፤ የቁርዓን የመጨረሻ አንቀፆች ለነብዩ መሃመድ የወረደበት ዕለት በመሆኑ በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ትልቅ በዓል እንደሆነ ተናግረዋል። የዘንድሮውን የአረፋ በዓል ልዩ የሚያደርገው ኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ እርምጃ ላይ በጀመረችበትና የሙስሊም ማኅበረሰቡ አንድነቱን ለማጠናከር የተነሳሳበት ወቅት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ ሙስሊም ወገኖች  'ኢድ ሙባረክ' ብለዋል። "የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት ለአገር አንድነት ጥንካሬ ነው" ያሉት ዶክተር አቢይ፤ አረፋ የመስጠት፣ የደግነትና የቸርነት በዓል በመሆኑ የተቸገሩና አንዳች ጥሪት የሌላቸውን ወገኖች በመርዳት በመልካምና ደግ ስራ በጋራ እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል። በአገሪቱ የአብሮነት ታሪክ ውስጥ የመቻቻል፣ መተዛዘንና መረዳዳት እሴት መላው የሙስሊም ማኅበረሰብ፣ አሁንም መንጋዎችን በመታገል አገርን በስርዓት የማቆም ደማቅ ታሪኩን በአብሮነት እንደሚያስቀጥል እምነታቸውን ገልጸዋል። ክፉ ተግባር በአንድ አካባቢና አጋጣሚ ብቻ በመከሰቱ ዝም ያለማለት ባህላችንን ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በጠንካራ መሰረት ላይ የማነጽ ታሪኩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራቸውን አስተላልፈዋል። ''እንደ ህግ አክባሪ ዜጋ መልካም ተግባርን የመውደድና ክፋትን የማውገዝ ሃላፊነት እንዳለብን ባለመዘንጋት የአገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ በመደመር ለማስቀጠል ሙስሊሙ የአገሬ ህዝብ የበኩሉን ሁሉ እንዲያደርግም ጥሪዬን አቀርባለሁ'' ብለዋል። ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የእምነት አባቶች ስርዓት አልበኝነት እንዳይሰለጥን ማህበረሰቡን በሞራልና በስነ ምግባር ተግተው እንዲያንጹ የጠየቁ ሲሆን፣ በዓሉ የበረከት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም