''አገር ስትነካ ስንቅ ማዘጋጀት ትንሽ አስተዋጾ ነው !'' የአሚር ኑር ወረዳ ነዋሪዎች

72

ሐረር፣ ኅዳር 2 /2014 (ኢዜአ)''አገሬ ስትነካ ስንቅ ማዘጋጀት ትንሹ አስተዋጾ ነው ፤ ለሀገር ፍቅርና ክብር የህይወት መስዋእትነት ይከፈላል" ያሉት በሐረሪ ክልል የአሚር ኑር ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ አበበች ዮሴፍ ናቸው።

አሸባሪው ህወሀት ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ እየተፋለሙ ላሉ መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች ጸጥታ ሀይሎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች  የሚገኙ ሴቶች ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነታቸውን ሲያረጋግጡ ቆይተዋል።

በቅርቡም መንግስት ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተከትሎ የስንቅ ዝግጅቱ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን የሀረሪ ክልል ሴቶችም ጥሪውን በመቀበል ስንቅ ማዘጋጀት ጀምረዋል ።

ወይዘሮ አበበች በክልሉ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ ከሚያዘጋጁ ሴቶች አንዷ ናቸው።

በራስ ተነሳሽነት እየተካሄደ ባለው ዝግጅት በመሳተፋቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

ወይዘሮ አበበች ለአገራቸው ባላቸው ፍቅር ስንቅ ማዘጋጀት ትንሹ አስተዋጽኦ መሆኑን ተናግረዋል።

''በወረዳው የምንገኝ ሴቶች በነቂስ በመውጣትና ስንቅ በማዘጋጀት ለአገሩ መስዋዕት እየከፈለ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነታችንን እየገለጽን ነው'' ሲሉም አክለዋል።

''በኢትዮጵያ ለመጣ እኔ ራሴ ሄጄ እዋጋለሁ ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ባንዲራችን ነች፤ ሕይወታችን ነች''ሲሉም አገርን ለማዳን መስዋትነት እንደሚከፍሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ መይሙና ሱፊያን ሌላዋ የስንቅ ዝግጅቱ ተሳታፊ ሲሆኑ ሴቶች ከስንቅ ዝግጅት በተጓዳኝ  ለሠራዊቱ ደም እየለገሱ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በቀጣይም ስንቁን እስከ ግንባር እንደሚያደርሱና ከተፈለገም ጠላትን እንደሚዋጉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሠራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

"የስንቅ ዝግጅቱ ለአገር ሉዓላዊነት እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት በአካባቢው ሴቶች ተነሳሽነትና መዋጮ እየተካሄደ የሚገኝ ''የኋላ ደጀንነት ነው'' ያሉት ደግሞ የሐኪም ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሰናይት ወንድወሰን ናቸው።

ለአገር ሉዓላዊነት መከበር ከፊት መቅደም ካለባቸው እንደማያመነቱ በመግለጽ።

ለጀግናው ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም አስታውቀዋል፡፡

ሌላዋ የስንቅ ዝግጅት ተሳታፊ ወይዘሮ ገነት ገብረማርያም ለሕይወቱ ሳይሳሳ ለአገር ሉአላዊነት እየተዋደቀ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ስንቅ በማዘጋጀታቸው ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

''የሠራዊቱ አባላት እናቶቻቸውና እህቶቻቸው ከጎናቸው መሆናችንን መረዳት ይገባቸዋል፤ አስፈላጊ ከሆነም ግንባር ድረስ በመሄድ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን''ብለዋል፡፡

ሕዝቡም ለአገር ደጀን ለሆነው ሠራዊት ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ሽብርተኞቹን ህወሃትና ጀሌዎቹን እየተፋለሙ ለሚገኙ  መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች ጸጥታ ሀይሎች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም