ህወሓት በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሃብት ውድመት አድርሷል

147

ባህር ዳር ህዳር 2/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈፀመባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ የሀብት ውድመት ማድረሱን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አንሙት በለጠ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት አሸባሪው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሰውና ህይወትና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል። 

አሸባሪው ህወሀት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለችግር እንዲጋለጥ ያደረገ ሲሆን 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል።

 በተጨማሪም እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ውሃ፣ መስኖ፣ መንገድ ያሉ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም የፍትህ፣ የፖሊስና መሰል የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መዝረፉንና ማውደሙን ገልጸዋል።

 ከዚህ ባሻገርም ንፁሃን ዜጎችን በጅምላ መግደሉን ጠቅሰው፣ የአርሶ አደሩን ሰብልና የቤት እንስሳትን ጭምር ማውደሙን አመልክተዋል። 

ሃላፊው እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ይሄን ያህል መጠን ያለው ጉዳት ማድረሱ የተረጋገጠው ወረራ በፈፀመባቸው የተለያዩ ዞኖች በሚገኙ 45 ወረዳዎች በተካሄደ ክልል አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ነው።

ዳሰሳ ጥናቱ አሸባሪው ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ በፀጥታ ሃይሉ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በለቀቃቸው አካባቢዎች የተደረገ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ በአሸባሪው ህወሓት ተወረው የሚገኙ አካባቢዎችን እደማያካትት ገልፀዋል።

 በጤናው ዘርፍ 1ሺህ 466 ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

 አሸባሪው በ6 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንዲሁም በ17 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ ባደረሰው ጉዳትም 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት መውደሙን ነው የገለጹት።

 "እንዲሁም በመንገድ መሰረተ ልማትና በድልድዮች ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት አስከትሏል" ያሉት አቶ አንሙት፤ በመስኖ ተቋምትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ሙሉ በመሉ ከጥቅም ውጭ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል። 

እነዚህ ከላይ ለማሳያ ይቅረቡ እንጂ የሽብር በድኑ በግብርና፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በገንዘብ፣ በውሃ ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ በንግድና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የከፋ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በግርድፉ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ279 ቢሊዮን 543 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት እንዲወድም ማድረጉን አቶ አንሙት አስታውቀዋል። 

በውድመቱም የሰዎች ሞት፣ አካላዊ ጉዳትና የስነልቦና ችግር፣ የሥራ መስተጓጎልና ምርታማነት መቀነስ መድረሱን ተናግረዋል።

በቀጣይ አዳዲስ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች የጉዳት መጠን ያካተተ ጥናት ሲካሄድ የጉዳቱ ስፋት በእጅጉ የከፋ እንደሚሆን ቢሮ ሃላፊው አመላክተዋል።

ከችግሩ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ተቋማትን መልሶ ስራ የማስጀመር ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ አንሙት እንዳሉት የደረሰው ውድመት ቢያንስ ከ10 እስክ 20 ዓመት ክልሉን በልማት ወደ ኋላ የሚጎትት ነው።

 "አሸባሪው ህወሓት ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳያደረስ አሁን በተጀመረው አግባብ ወራሪውን መደምሰስ ይገባል" ብለዋል። 

በቀጣይ በክልሉ በሚከሄደው የመልሶ ግንባታ ስራ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የፌደራል መንግስት፣ ዳያስፖራው፣ መላ ህብረሰቡና ባለሃብቱ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

 የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ወንድወሰን አቢ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሀት በወረራቸው አካባቢዎች በ1 ሺህ 660 ትምህርት ቤቶች ላይ ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት አድርሷል።  

ባደረሰው ጉዳትም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውንና 47 ሺህ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችም ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በገንዘብ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት መውደሙን ጠቅሰው፣ "የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የተለያዩ ተቋማት፣ ባለሃብቶችና ግለሰቦች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ" ብለዋል። 

ወራሪው ካደረሰው ውድመት ስፋት አንፃር የተገኘው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ችግሩ ጠንካራ የሃብት ማሰባሰብ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

 "አሸባሪው ህወሀት በፈጸመው ወራራ የንፋስ መውጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዳግም ለአገልግሎት እንዳይበቃ በሚያደርግ ደረጃ ጉዳት አድርሶበታል" ያሉት ደግሞ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሙሉ ናቸው። 

ወራሪው በሆስፒታሉ ያሉ የሕክምና መሳሪያዎችን የቻለውን ዘርፎ፤ ያልቻለውን ደግሞ አውድሞ መሄዱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም