የግል መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ሊሰሩ ይገባል

134

 ህዳር 2/2014 (ኢዜአ) የግል መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።

ለንግድ አገልግሎት የተቋቋሙ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት አገሪቷ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ሳያገናዝቡ እየሰሩ መሆኑን ባለስልጣኑ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ብዙዎቹ የግል መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተገንዝበው ለዚያ የሚመጥን ሥራ እየሰሩ አይደለም፡፡

መገናኛ ብዙኃኑ ከዚህ በፊት ከተለመደው አሰራር እና የአዘጋገብ ስልት ወጥተው ኢትዮጵያና ዜጎቿን ከገጠሙት ወቅታዊ ችግሮች ሊያሻግሩ በሚችሉ ዘገባዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብለዋል።

የህዝብ ሚዲያዎች በአንፃራዊነት በአገራዊ ህልውናው የተሻሉ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው የግል መገናኛ ብዙሃንም ለአገራቸውና ህዝባቸው ወግነው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በመዝናኛው ዘርፍ የተሰማሩ ሚዲያዎችም ቢሆኑ አገራዊ አንድነትና አብሮነትን የሚያጠናክሩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን በማቅረብ ዜጎች ለአገራቸው እንዲነሳሱ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አገር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስትገባ ወቅቱን የሚመጥን ሥራ በማከናወን ረገድ ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

ለውጭ ሚዲያዎች ወኪል በመሆን በአገር ውስጥ የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎችም ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው የአገራቸውን እውነታ ለዓለም ማሳወቅ ይኖርባቸዋልም ብለዋል፡፡

እነዚህ ባለሙያዎች አገራቸውን በተመለከተ የሚነዙ የውሸት ፕሮፓጋንዳዎችን መቃወም እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይህን በመሥራትም ለኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ለውጭ ሚዲያዎች ወኪል ሆነው የሚሰሩ ጋዜጠኞች አገር ከምንም በላይ በመሆኗን በቅጡ ተረድተው የህዝቡን ስነ-ልቦና፣ ማንነትና ታሪክ ጠብቀው የኢትጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ ሥራ ላይ ባለመሳተፍ አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እንድትወጣ ከመንግሥትና ከህዝብ ጎን በመሆን የተጀመረውን ጥረት መደገፍ የሁላችንም ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም