ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን በአገር ውስጥ በማልማት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረት እየተሰራ ነው

183

ህዳር 1/2014 (ኢዜአ) ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑትን ጨምሮ ሌሎችም ማዕድናትን በአገር ውስጥ በማልማት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገልጿል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ድሬዳዋ የሚገኘውን የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የምርት ሂደትና የስራ  እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

ከጉብኝታቸው በኋላ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ማዕድናት ያላት በመሆኗ በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማዳን ይቻላል ብለዋል።

ከሰሞኑ የአራት የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የስራ እንቅስቃሴ መጎብኘታቸውንና ፋብሪካዎቹ በአገር ውስጥ የተመረተ የድንጋይ ከሰል ምርት መጠቀም በመጀመራቸው ምርታማነታቸው መጨመሩን ገልጸዋል።

መንግስት የሲሚንቶን ምርት ለማሳደግ እየሰራ ባለው ማሻሻያ ፋብሪካዎች በቀን የሚያመርቱት ምርት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለይም የሲሚንቶ አምራቾች ለግብዓትነት የሚጠቀሟቸው ከውጭ የሚገቡ እንደ ድንጋይ ከሰል ያሉ የማዕድን ምርቶች በአገር ውስጥ መሸፈኑ ለምርቱ መጨመር ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በቀጣይም የድንጋይ ከሰል አቅርቦቱን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በማዕድን ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን በአገር ውስጥ በማልማት ለመጠቀምና በቀጣይም ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።

በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እንደሚቻል ነው ያነሱት።

የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ተወካይ አቶ ፍፁም ንጉሴ ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ እየተጓዘች ቢሆንም የልማት ስራዎች ሳይቋረጡ እየሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ መደበኛ ስራውን በተሳለጠ መንገድ እየከወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የሚስተዋለውን የሲሚንቶ ምርት እጥረት በማቃለል ፍላጎቱን ለመሙላት እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም