የህልውና ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል

61

ሀዋሳ፤ ህዳር 1/2014 (ኢዜአ) በሀገር ላይ የተቃጣውን ጥቃት በመመከት የህልውና ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት አስታወቁ።

በክልሉ  የሚንቀሳቀሱ 12 ክልላዊና ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው  የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል ።

የጋራ ምክር ቤቱ  በመግለጫው  እንዳመለከተው ፤  ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤትና በሀገረ መንግስት ግንባታ ቀደምት ናት።

በተለይ በህዝቦቿ ጀግንነት፣ አንድነትና አልበገር ባይነት ነጻነቷ ተከብሮ የኖረችው ኢትዮጵያ የአፍሪካና የሌሎች ጥቁር ህዝቦች  የድል ማሳያ  መሆኗን በመግለጫው ተወስቷል።

ይህንን የዘነጋው እና ከደርግ ውድቀት ወዲህ ስልጣን የተቆጣጠረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሀገር የመበተን የረጅም ዘመናት ህልሙን ለማሳካት በከፋፍለ ግዛ መርህ አንድነትን ለመሸርሸር ሲሰራ ቆይቷል ነው ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ።

በተለይ  በዚህ ሂደት ዜጎችን ለከፋ ሰቆቃና ጭቆና ማድረጉን ታሪክ አይዘነጋውም ብሏል።

በህዝብ ተጠልቶ ከስልጣን ከተባረረ በኋላ መቀሌ በመመሸግ በመንግስት የተሰጠውን የሰላም ዕድል ባለመጠቀም የሀገር መከላከያ ሰሜን ዕዝን  በማጥቃት ጭምር ሀገርን ለመበተን ያለውን ዓላማ ግልጽ አድርጓል።

ከጥፋቱ የመማር ስብዕና የሌለው  አሸባሪው ቡድን ከኢትዮጵያ ጫንቃ ለአንዴና ለመጨረሻ ተወግዶ እንዲቀበር መላው ዜጋ የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ የአይበገርነት ክንዱን እንዲያሳርፍ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

መግለጫውን  ያቀረቡት በምክር ቤቱ የሚዲያ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ደመላሽ አበራ፤ በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች  የጋራ ምክር ቤት አባላት ጦርነትን ለመመከትና እናት ሀገርን ከወራሪው ለመታደግ አስፈላጊውን መስዋዕትነት  ለመክፈል ወስነው መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ከዓለም አቀፍ መርህ ባፈነገጠ መልኩ ለአሸባሪው  ያላቸውን ወገንተኝነት በግልጽ በማሳየት ታሪካዊ ስህተት እየፈጸሙ ያሉት   አሜሪካ ጨምሮ  አንዳንድ የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ምክር ቤቱ ማሳሰቡን ጠቅሰዋል።

በሀገር ላይ የተቃጣው ጦርነት  በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ እንዲቻል መላው ዜጋ በግንባር እየተፋለመ የሚገኘውን መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ጎን እንዲሰለፍ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

በክልሉና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ እናቶችና እህቶች ወንበዴውን ቡድን ከነግብረአበሮቹ ለመቅበር በሚደረገው ፍልሚያ ለመከላከያ ስንቅ በማዘጋጀትና አቅም በፈቀደ ሁሉ እንድተባበሩም እንዲሁ።

በተለይም ወጣቱ ሃይል የአካባቢውን ሠላም በንቃት በመጠበቅ የጥፋት ቡድኑ የሚያሰማራቸው ተላላኪዎችንና ባንዳዎች በማጋለጥ ሴራቸውን ለማክሸፍ ሃላፊነቱን እንዲወጣ በመግለጫው ተመላከቷል።

ጀግኖች የቀድሞ ሰራዊት አባላት በአሸባሪው ህወሃት  የተፈጸመባቸው በደል ታሪክ እንደማይረሰው ያወሳው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ ወንበዴውን በተባበረ ክንዳቸው በመደምሰስ ሂደት በግንባር ቀደምነት በመሰለፍ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

ሀገሪቱ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደችው አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውጤትን ወደ ጎን በመተው ከጠላት ተልዕኮ በመቀበል የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን የሚሉ ቀብጸ ተስፋዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ የኋላሸት በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ ሀገር ከገጠማት ችግር በአጭር ጊዜ ለተላቃ ፊቷን ወደ ልማት እንድትመለስ ከፓርቲ አጥር ወጥተን ለህልወና ዘመቻው በጋራ ልንሰለፍ ይገባል ብለዋል።

ሁሉም ፓርቲዎች አባሎቻቸውን በማስተባበር የአካባቢን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ መከላከያ ሰራዊት ለማጠናከርና  እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት ቁርጠኛ መሆናችንን በምክር ቤቱ  አረጋግጠናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም