አሸባሪውን ሕወሃት በተባበረ ክንድ ለማጥፋት ኢትዮጵያዊያን በጀግንነት እየተፋለሙት ነው

80

ህዳር 1/2014 (ኢዜአ) አሸባሪውን ሕወሃት በተባበረ ክንድ ለማጥፋት ኢትዮጵያዊያን በጀግንነት እየተፋለሙት መሆኑን በዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር ግንባር በመፍጠር አገር ለማፍረስ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አለሙ፤ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተፋለሙት መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመውጋት የአገር ክህደት ከፈፀመ በኋላ ዜጎችን በመግደልና ንብረት በማውደም ጥፋቱን ቀጥሎበታል።

ከማይካድራ እስከ ጭና እንዲሁም በአፋር እና ሌሎች አካባቢዎችም ከህፃን አስከ አዋቂ በመግደል የጭካኔ ጥጉን አሳይቷል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን ሃይል በተባበረ ክንድ ለማጥፋት በቆራጥነት እየተፋለሙት መሆኑን ዶክተር አለሙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አሸባሪውን በየደረሰበት ሁሉ ረመጥ ሆነው እያቃጠሉት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ዳር ድንበር፣ ሉአላዊነትና ክብር ድርድር አያውቁም ያሉት ዶክተር አለሙ አሸባሪው ከገባበት እንዳይወጣ እየተፋለሙት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪዎቹን ህወሃትና ሸኔ በአጭር ጊዜ ለማጥፋት የጋራ ክንዳችን በድል አድራጊነቱ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የሽብር ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያደርስበት ብርቱ ምት ኢትዮጵያዊነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም