የአካባቢያችንን ሠላም ነቅተን በመጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው

58

ሀዋሳ ፤ ህዳር 1/2014 (ኢዜአ) ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የአካባቢያቸውን ሠላም ነቅተው በመጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የከተማዋ ነዋሪ  ወጣት አብዱልከሪም ሰይድ፤  የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት ለመገዳደር  የውስጥና የውጭ  ጠላቶች ተባብረው መነሳታቸው   ቁጭት እንዳሳደረበት ለኢዜአ ተናግሯል።

በሀገር ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መነሳሳቱን አሰታውቋል።

የጥፋት ተላላኪዎቹን ወደ ከተሞች በመላክ ህዝብ የሚያሸብር ተግባር  አሸባሪው ህወሓት የተካነበት  የሽፍታ ባህሪው መሆኑን ጠቅሷል።

በግንባር ያለውን የህልውና  ዘመቻ  ከመደገፍ ባሻገር ሁሉም አካባቢውን  በመጠበቅ የሀገርን  ሠላም ማረጋገጥ ከሁሉም ዜጋ እንደሚጠበቅም ጠቁሟል።

እሱን ጨምሮ የአካባቢው  ወጣቶች  ከከተማው የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢያችን ሠላም በንቃት እየጠበቁ እንደሚገኝ ተናግሯል።

 የሀገርን ሠላም ማስጠበቅ የምንችለው ጉዳዩን ለመንግስት ብቻ ሳንተው ሁላችንም ያለንበትን አካባቢ ሠላም መጠበቅ ስንችል ነው ያሉት ደግሞ መምህር መሐሙድ ሁሴን ናቸው።

የተሰጣቸውን ሙያዊ ሃላፊነት ከመወጣት ባለፈ  ማህበረሰቡን በማንቃት የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት ዳግም በህዝቡ ላይ የጭቆና ቀንበር ለመጫን ካለው ህልም የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ማወጁን አውስተዋል።

ወይዘሮ ሶፊያ አደም በበኩላቸው፤  በግንባር እየተዋደቁ ላሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ሁላችንም የሰላም ማስከበሩ አካል መሆን  እንደሚገባ  ሀገራዊ ሁኔታው ያስገድደናል'' ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ በገባባቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች በንፁሀን ዜጎች ላይ የፈፀመው ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በሌሎች አካባቢዎች እስኪደገም መጠበቅ የለብንም ነው ያሉት።

''በአካባቢያችን እንግዳ የሆኑ እንቅስቃሴዎችንና ፀጉረ ልውጦችን በንቃት በመከታተል  እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅብናል'' ብለዋል።

ሰሞኑን በደሴና አካባቢው በሰርጎ ገቦችና ከማህበረሰቡ ጋር ተመሳስለው በኖሩ የጥፋት ተልኮ አስፈፃሚዎች የደረሰው ጉዳት ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባ አስተማሪ ክስተት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ሙስጠፋ ረዲ ናቸው።  

መስል ድርጊቶች  በአካባቢያቸው እንዳይደገም  ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ነቅተው እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 አሸባሪው ህወሓትን እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሀዝባዊ ሰልፍ ሰሞኑን  በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ   በተካሄደበት ወቅት  በግንባር እየተዋደቁ ላሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካለት 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ከህዝቡ መበርከቱን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም