የድንጋይ ከሰል አቅርቦትን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመሸፈን እየተሰራ ነው

247

ጥቅምት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድንጋይ ከሰል አቅርቦትን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በመሸፈን የሲሚንቶ ምርት ዋጋ እንዲቀንስ እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ በደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተገኝተው የሲሚንቶ ምርት ሂደቱና አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ተመልክተዋል።

መንግስት የሲሚንቶ ምርትን ለመጨመር እየሰራ ባለው የማሻሻያ በአገሪቱ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በቀን የነበረው የምርት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለይም የሲሚንቶ አምራቾች ለግብዓትነት የሚጠቀሟቸው ከውጭ የሚገቡ እንደ ድንጋይ ከሰል ያሉ የማዕድን ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሲሚንቶ ፋሪካዎች በአገር ውስጥ የተመረተ የድንጋይ ከሰል ምርት መጠቀም የጀመሩ መሆኑን ገልጸው፤ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካም ይህን በማድረግ ምርቱን እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ማዕድናት እንዳላት ጠቅሰው፤ ይህንን ሀብት በሰፊው በመጠቀም ለአገር ግንባታ የጀርባ አጥንት ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በሲሚንቶ ምርት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመድፈን ምርትን ለመጨመርና የግብይት ሰንሰለትን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

“ከውጪ ይገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ በመተካት የሲሚንቶ ምርት እንዲጨምርና ዋጋም እንዲቀንስ ለማድረግ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የድንጋይ ከሰል አቅርቦትን በአገር ውስጥ መሸፈን በመቻሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሲሚንቶ ምርቱ እየጨመረ እንደሚገኝ አንስተው፤ የድንጋይ ከሰል የማዕድን ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የመተካት ሂደት ከወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል።

የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አለማየሁ በበኩላቸው የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል የማዕድን ግብአቶችን በመጠቀም የማምረት አቅምን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

“በዚህ ምክንያት ፋብሪካው በሙሉ አቅም ማምረት በመጀመሩ የሲሚንቶ ዋጋ እንዲቀንስ ሆኗል” ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም