ኢትዮጵያን ለማዳን የተላለፈውን የክተት ጥሪ ተቀብለን ለመዝመት ተዘጋጅተናል

89

ፍቼ፣ነገሌ/ ጥቅምት 30/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያን ለማዳን በመንግስት የተላለፈውን የክተት ጥሪ ተቀብለን ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅተናል ሲሉ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋና ጉጂ ዞኖች የሚገኙ የሚሊሻ አባላትና ወጣቶች ገለጹ።

በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ የሚገኙ የሚሊሻ አባላት ለኢዜአ እንደገለፁት ለሀገራቸው ክብርና ነፃነት መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተዋል፡፡

የወረዳው የወርጡ ቀበሌ ታጣቂ አቶ ዮሐንስ ከበደ አሸባሪዎቹ የህወሀትና ሸኔ በሀገር ህልውና ላይ የጋረጡትን አደጋ ለመመከት ወደ ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ሀገርን ለማዳን ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው የሽብርተኞችን እንቅስቃሴ ለመግታት ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

"የክተት ጥሪውን ተቀብዬ ወደ ግንባር በመዝመት የጋራ ጠላት የሆኑትን  ህወሀትና ሸኔን  ለመደምሰስ  ተዘጋጅቻለሁ " ያሉት ደግሞ በወረዳው የኮትቾ ሶፋኔ ቀበሌ ነዋሪና ዕድሜያቸው 54 ዓመት የሆኑት አቶ ግርማ ጌታቸው ናቸው።

"አሸባሪዎች የብዙሀን ሀገር የሆነችውን እናት ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ለማዋረድና ለማሳጣት በሀሰት የሚያደርጉት ስም የማጥፋት ስራ እጅግ አሳዝኖኛል " ሲሉ የአሸባሪዎቹን ድርጊት ኮንነዋል ።

የቶርባን አሼ ቀበሌ ታጣቂ አቶ መርሻ አደሬም "ህወሀትና ሸኔን  ለመደምሰስ ሁሉም በቁጭትና በእልህ ሊነሳ ይገባል" ብለዋል ።

ለጠላት ጊዜ ሳይሰጡ የህልውና ዘመቻውን በአሸናፊነት ለመወጣት የክተት ጥሪውን እንደተቀበሉ ገልጸዋል፡፡

የግራር ጃርሶ ወረዳ የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ታከለ ከወረዳው 21 ገጠር ቀበሌዎች የተውጣጡ የአካባቢ ሚሊሻ አባላት የክተት ጥሪውን ተቀብለው በህልውና ዘመቻው ለመሳተፍ ወደ ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን  ተናግረዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ወደ ግንባር በመሄድ ድል ለመቀዳጀት የሚያስችላቸውን የመከላከል፣ የማጥቃትና ከፍተኛ ጀብዱ የመፈጸም ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውቀዋል ።

በተመሳሳይ ለሀገር ሉአላዊነት መከበር በመንግስት የቀረበውን የክተት ጥሪ የተቀበሉ የነገሌ ከተማ ወጣቶች ወደ ግንባር ለመዝማት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በነገሌ ከተማ  የቀበሌ 03 ነዋሪ ወጣት መብራቱ ከበደ ሽብርተኛው ህወሀት በስልጣን በቆየባቸው 27 አመታት የመብት ጥያቄ ባቀረቡ የኦሮሞ ወጣቶች ላይ ያደረሰውን ግፍና መከራ በምሬት አስታውሷል፡፡

አሸባሪው ህወሀት ያ ሁሉ አልበቃ ብሎት አሁን ደግሞ ሀገር ለማፍረስ ተላላኪውን ሸኔን በማሰለፍ ጭምር በንጽሃን ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ መሆኑን ገልጾ  "ሀገር ለማዳንና ንጹሃንን ለመታደግ ተደራጅተን ከመዝመት  ሌላ አማራጭ የለንም" ብሏል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ሁሴን ሳኖ በበኩሉ ሽብርተኛው ህወሀት ከኢትዮጵያ ህዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ መነሳቱ አሳዛኝም አሳፋሪም መሆኑን ገልጿል፡፡

"ሽብርተኛውን ህወሀት በሚደግፉ ምእራባዊያን ጫናና ተጽእኖ የሀገሩን ሉአላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ በታሪክ የለም፤ አሁንና ወደ ፊትም አይኖርም" ብሏል፡፡

"አባቶቻችን የህይወት መስዋእትነት ከፍለው የውጭ ወራሪዎችን አሳፍረው በመመለስ በአድዋና በካራማራ የሰሩት ታሪካዊ ድል በእኛም ዘመን ይደገማል"ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት መንግስት ሀገርን ለማዳን ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው ለመዝመት ተዘጋጅተዋል።

የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ  "የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን በመመከት ከመቸውም ጊዜ በላይ ሀገር የማዳን ታሪካዊ ሀላፊነት ወድቆብናል" ብለዋል፡፡

ወጣቱ የክተት ጥሪ ተቀብሎ ሽብርተኞቹን ህወሀትና ሸኔን በመመከት የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም