የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ስራዎቻችን እውን የሚሆኑት አገር ስትኖር ነው

ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ) የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ስራዎቻችን እውን የሚሆኑት አገር ስትኖር በመሆኑ ለሕልውናዋ መከበር የድርሻችንን ማበርከት ይጠበቅብናል ሲሉ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው ለአገር መከላከያ ሠራዊት 15 ሚሊዮን ብር እና ግምታቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሆኑ 30 ሰንጋዎች አበርክቷል።

ለአገር መከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ተቋማትና ግለሰቦች ዛሬ የገንዘብና የስንቅ ድጋፍ አደርገዋል።

ኅብረት ኢትዮጵያ የስራ ስምሪት 500 ሺህ ብር፣ አልማዝ ኤሌክትሮኒክስ 250 ሺህ ብር፣ አቶ አብዩ እና እንዳለ 100 ሺህ ብር፣ አቶ ሰለሞን እምሩ በወላጆቻቸው ስም 10 ሺህ እና በወንድማችን ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ ስም 10 ሺህ እንዲሁም አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የደረቅ ስንቅ ድጋፍ አድርገዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ የመማር ማስተማር እና ሌሎችም ስራዎቻችን  እውን የሚሆኑት አገር ስትኖር በመሆኑ ሊያፈርሳት የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ እንደ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር በአገር ሕልውና ላይ የደቀነውን አደጋ በጋራ እንደሚመክቱም አረጋግጠዋል።

አሜሪካና ሌሎች ምዕራባዊያን አገራት አሸባሪውን ቡድን በመጠቀም የራሳቸውን ጥቅም ለማስፈጸም የሚያደርጉት ጥረት ምንም ተቀባይነት የለውም ሲሉም አክለዋል።

የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዱዓለም እና የቀድሞ ሠራዊት አባል ሻለቃ ተፈራ ንጉሴ በበኩላቸው አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል እኛም የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ከሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ ከፍተኛ ሞራል መሆኑን ተናግረዋል።

የሕልውናው ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም